በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 24

ሌባ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!

ሌባ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!

አንድ ሰው ዕቃህን ሰርቆህ ያውቃል?— እንደሰረቀህ ስታውቅ ምን ተሰማህ?— የሰረቀህ ሰው ሌባ ነው፤ ሌባን ደግሞ ማንም አይወደውም። አንድ ሰው ሌባ የሚሆነው እንዴት ነው? ሌባ የሚሆነው ሌባ ሆኖ ስለሚወለድ ነው?—

ሰዎች ኃጢአተኞች ሆነው እንደሚወለዱ ተምረናል። ስለዚህ ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን ነን። ሆኖም ማንም ሰው ሌባ ሆኖ አይወለድም። አንድ ሌባ የሆነ ሰው ጥሩ ቤተሰብ ያሳደገው ሊሆን ይችላል። ወላጆቹ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ ታማኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለገንዘብና በገንዘብ ለሚገዙ ነገሮች ያለው ምኞት ሌባ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል።

የመጀመሪያው ሌባ ማን ይመስልሃል?— እስቲ ማን እንደሆነ ለማሰብ እንሞክር። ታላቁ አስተማሪ በሰማይ ሳለ ይህን ሌባ ያውቀዋል። ይህ ሌባ መልአክ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ሁሉንም መላእክት ፍጹማን አድርጎ ስለፈጠራቸው ይህ መልአክ ሌባ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?— በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ እንደተማርነው ይህ መልአክ የራሱ ያልሆነውን ነገር ተመኘ። የተመኘው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከፈጠረ በኋላ ይህ መልአክ አዳምና ሔዋን እሱን እንዲያመልኩት ፈለገ። ሆኖም ይህ አምልኮ ለእሱ የሚገባ አልነበረም። የእነሱ አምልኮ የሚገባው ለአምላክ ነው። ይህ መልአክ ግን ለአምላክ የሚገባውን አምልኮ ሰረቀ! አዳምና ሔዋን እሱን እንዲያመልኩት በማድረግ ሌባ ሆነ። በዚህ መንገድ ሰይጣን ዲያብሎስ ሆነ።

አንድን ሰው ሌባ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?— የራሱ ያልሆነውን ነገር ለማግኘት ያለው ምኞት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ምኞት በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ጥሩ ሰዎችንም እንኳን መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌባ የሆኑ ሰዎች ይህን መጥፎ ድርጊት  ትተው ጥሩ ነገር ለመሥራት ፈቃደኞች አይሆኑም። ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች አንዱ የኢየሱስ ሐዋርያ ነበር። ስሙ የአስቆሮቱ ይሁዳ ይባላል።

ይሁዳ ከልጅነቱ ጀምሮ የአምላክን ሕግ የተማረ ስለነበረ መስረቅ ስህተት መሆኑን ያውቃል። እንዲያውም አምላክ በአንድ ወቅት ከሰማይ ሆኖ ሕዝቡን “አትስረቅ” የሚል ሕግ እንደሰጣቸው ያውቃል። (ዘፀአት 20:15) ይሁዳ አድጎ ትልቅ ሰው ሲሆን ከታላቁ አስተማሪ ጋር ተገናኘና የእሱ ደቀ መዝሙር ሆነ። እንዲያውም በኋላ ኢየሱስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ እንዲሆን መርጦታል።

ኢየሱስና ሐዋርያቱ ከቦታ ወደ ቦታ የሚጓዙት አንድ ላይ ነበር። ምግባቸውንም አንድ ላይ ሆነው ይመገቡ ነበር። ሁሉም ገንዘባቸውን በአንድ ሣጥን ያስቀምጡ ነበር። ኢየሱስ፣ ሣጥኑን እንዲይዝ ኃላፊነት የሰጠው ለይሁዳ ነበር። በእርግጥ፣ ሣጥኑ ውስጥ ያለው ገንዘብ የይሁዳ አልነበረም። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሁዳ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?—

ይሁዳ የሰረቀው ለምን ነበር?

ይሁዳ ሳያስፈቅድ ከሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ መውሰድ ጀመረ። ገንዘቡን በድብቅ ይወስድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ ገንዘብ መውሰድ የሚችልበትን መንገድ ይፈልግ ነበር። ሁልጊዜ የሚያስበው ስለ ገንዘብ ሆነ። ይህ መጥፎ ምኞቱ ታላቁ አስተማሪ ከመገደሉ ከጥቂት ቀናት በፊት ምን እንዳስከተለ እንመልከት።

የኢየሱስ ጓደኛ የነበረው የአልዓዛር እህት ማርያም ምርጥ የሆነ ሽቶ አመጣችና በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰችው። ይሁዳ ግን በዚህ አጉረመረመ። ያጉረመረመው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ለዚህ ያቀረበው ምክንያት ሽቶው ተሽጦ ገንዘቡ ለድሆች ሊሰጥ ይገባል የሚል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይሁዳ ለመስረቅ እንዲመቸው ብዙ ገንዘብ ወደ ሣጥኑ እንዲገባ ፈልጎ ነበር።—ዮሐንስ 12:1-6

ኢየሱስ ጥሩ ነገር ያደረገችውን ማርያምን እንዳያስቸግራት ለይሁዳ ነገረው። ይሁዳ፣ ኢየሱስ እንዲህ ሲለው ደስ አላለውም፤ ስለዚህ የኢየሱስ ጠላቶች ወደነበሩት ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነሱም ኢየሱስን ሊይዙት ፈለጉ፤ ሆኖም ሰው እንዳያያቸው ሲሉ በሌሊት ሊይዙት ወሰኑ።

 ይሁዳ ካህናቱን ‘ገንዘብ ከሰጣችሁኝ ኢየሱስን እንዴት ልትይዙት እንደምትችሉ እነግራችኋለሁ። ምን ያህል ገንዘብ ትሰጡኛላችሁ?’ አላቸው።

ካህናቱም ‘ሠላሳ የብር ሳንቲሞች እንሰጥሃለን’ አሉት።—ማቴዎስ 26:14-16

ይሁዳ ገንዘቡን ተቀበለ። ታላቁን አስተማሪ ለእነዚህ ሰዎች እንደሸጠላቸው ያህል ነበር! እንዲህ ዓይነት ክፉ ሥራ የሚሠራ ሰው አይገርምህም?— አንድ ሰው ሌባ ከሆነና ገንዘብ መስረቅ ከጀመረ እንዲህ ዓይነት ድርጊት መፈጸሙ አይቀርም። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከማንም በላይ ሌላው ቀርቶ ከአምላክም እንኳን አስበልጦ ገንዘብን ይወዳል።

ምናልባት ‘ከይሖዋ አምላክ አስበልጬ የምወደው ምንም ነገር የለም’ ብለህ ትናገር ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ መሆኑ ጥሩ ነው። ኢየሱስ ይሁዳን ሐዋርያ አድርጎ በመረጠው ጊዜ ይሁዳም እንዲህ ዓይነት ስሜት የነበረው ሰው ሊሆን ይችላል። ሌባ የሆኑ ሌሎች ሰዎችም በአንድ ወቅት አምላክን ከሁሉ ነገር አስበልጠው እንደሚወዱ አድርገው ያስቡ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

አካንና ዳዊት ምን መጥፎ ነገር እያሰቡ ነው?

ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ፣ የአምላክ አገልጋይ የነበረው አካን ሲሆን ይህ ሰው ታላቁ አስተማሪ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ይኖር የነበረ ነው። በአንድ ወቅት አካን የሚያምር ልብስ፣ ወርቅና የብር ሳንቲሞች አየ። እነዚህ ነገሮች  የእሱ አልነበሩም። እነዚህ ነገሮች ከአምላክ ሕዝብ ጠላቶች የተወሰዱ ስለነበሩ የይሖዋ ንብረቶች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አካን ግን እነዚህን ነገሮች ለማግኘት በጣም ስለተመኘ ሰርቆ ወሰዳቸው።—ኢያሱ 6:19፤ 7:11, 20-22

ሌላው ምሳሌ ደግሞ የሚከተለው ነው። በድሮ ጊዜ ይሖዋ ዳዊትን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ንጉሥ እንዲሆን መርጦት ነበር። አንድ ቀን ዳዊት ቤርሳቤህ የምትባል ቆንጆ ሴት መመልከት ጀመረ። ሲመለከታት ቆየና ሚስቱ እንድትሆን ወደ ቤቱ ሊወስዳት አሰበ። ይሁን እንጂ እሷ የኦርዮ ሚስት ነበረች። ዳዊት ምን ማድረግ ነበረበት?—

ዳዊት ቤርሳቤህን የራሱ ሚስት አድርጎ ለመውሰድ ማሰቡን መተው ነበረበት። እሱ ግን አልተወም። ስለዚህ ዳዊት ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚያም ኦርዮን አስገደለው። ዳዊት እነዚህን መጥፎ ነገሮች ያደረገው ለምንድን ነው?—  የሌላ ሰው ሚስት የሆነችን ሴት ለራሱ ለመውሰድ መመኘቱን ስለቀጠለ ነው።—2 ሳሙኤል 11:2-27

አቤሴሎም ሌባ የነበረው በምን መንገድ ነው?

ዳዊት በፈጸመው ድርጊት በጣም ስላዘነ ይሖዋ በሕይወት እንዲኖር ፈቀደለት። ይሁን እንጂ ዳዊት ከዚያ በኋላ ብዙ ችግር ደረሰበት። ልጁ አቤሴሎም የዳዊትን የንጉሥነት ቦታ ለመውሰድ ተመኘ። ስለዚህ ሰዎች ወደ ዳዊት ሲመጡ አቤሴሎም አቅፎ ይስማቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ አቤሴሎም “የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ” ይላል። አቤሴሎም ሰዎቹ በዳዊት ፋንታ እሱ ንጉሣቸው እንዲሆን እንዲመኙ አደረገ።—2 ሳሙኤል 15:1-12

አንተም እንደ አካን፣ እንደ ዳዊትና እንደ አቤሴሎም አንድ ነገር በጣም ተመኝተህ ታውቃለህ?— የተመኘኸው ነገር የሌላ ሰው ከሆነ ያንን ነገር ያለ ፈቃድ መውሰድ ሌብነት ነው። የመጀመሪያው ሌባ የሆነው ሰይጣን ምን እንደተመኘ ታስታውሳለህ?— ሰዎች አምላክን ከማምለክ ይልቅ እሱን እንዲያመልኩት ተመኘ። ስለዚህ ሰይጣን አዳምና ሔዋን እሱን እንዲታዘዙት ባደረገ ጊዜ ስርቆት ፈጽሟል።

አንድ ሰው አንድ ነገር ካለው ያንን ነገር ማን ሊጠቀምበት እንደሚገባ የመወሰን መብት አለው። ለምሳሌ ያህል፣ ከሌሎች ልጆች ጋር ለመጫወት ቤታቸው ትሄድ ይሆናል። ወደ ቤትህ ስትመለስ ከእነሱ ቤት አንድ ነገር ብትወስድ ተገቢ ነው?— የልጆቹ አባት ወይም እናት ካልፈቀዱልህ በቀር ምንም ነገር መውሰድ የለብህም። እነሱን ሳትጠይቅ ምንም ነገር ብትወስድ ሌብነት ነው።

አንድን ነገር ለመስረቅ የምትፈተነው ለምን ሊሆን ይችላል?— ለመስረቅ የምትፈተነው የአንተ ያልሆነውን ነገር ስትመኝ ነው። ስትሰርቅ ሌላ ሰው ባያይህ እንኳ ማን ያይሃል?— ይሖዋ አምላክ ያይሃል። አምላክ ደግሞ ስርቆትን እንደሚጠላ ማስታወስ ይኖርብናል። ስለዚህ ለአምላክና ለሰው ፍቅር ካለህ ፈጽሞ ሌባ እንዳትሆን ይረዳሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ መስረቅ ስህተት መሆኑን በግልጽ ይናገራል። እባካችሁ ማርቆስ 10:17-19፤ ሮም 13:9 እና ኤፌሶን 4:28ን አንብቡ።