በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 29

ሁሉም ዓይነት ግብዣ አምላክን ያስደስተዋል?

ሁሉም ዓይነት ግብዣ አምላክን ያስደስተዋል?

አምላክ በዚህ ግብዣ የተደሰተው ለምን ነበር?

በግብዣ ላይ መገኘት ያስደስትሃል?— ግብዣዎች አስደሳች ሊሆኑ ይችላሉ። ታላቁ አስተማሪ ወደ ግብዣ እንድንሄድ የሚፈልግ ይመስልሃል?— ኢየሱስ ግብዣ ተብሎ ሊጠራ በሚችል የአንድ ሰው ሠርግ ላይ ተገኝቷል፤ ከደቀ መዛሙርቱም መካከል አንዳንዶቹ አብረውት ሄደዋል። ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ስለሆነ ጥሩ በሆኑ ግብዣዎች ላይ ተገኝተን ስንደሰት እሱም ደስ ይለዋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ ዮሐንስ 2:1-11

በዚህ መጽሐፍ ገጽ 29 ላይ ይሖዋ ቀይ ባሕርን ከፍሎ እስራኤላውያንን እንዳሻገረ ተመልክተን ነበር። ይህ ታሪክ ትዝ ይልሃል?— ሕዝቡ ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላ የዘፈኑና የጨፈሩ ከመሆኑም በላይ ለይሖዋ ምስጋና አቅርበዋል። ይህም እንደ ግብዣ ነበር። ሕዝቡ በጣም ተደስተው የነበረ ሲሆን አምላክም እንደተደሰተ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዘፀአት 15:1, 20, 21

ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ እስራኤላውያን ወደ ሌላ ትልቅ ግብዣ ሄደው ነበር። በዚህ ጊዜ ግን የጋበዟቸው ሰዎች ይሖዋን እንኳ የማያመልኩ ነበሩ። እንዲያውም የጋበዟቸው ሰዎች ለሌሎች አማልክት የሚሰግዱና ካላገቡት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ነበሩ። ወደዚህ ዓይነት ግብዣ መሄድ ተገቢ ይመስልሃል?— እስራኤላውያን ወደዚህ ግብዣ በመሄዳቸው ይሖዋ አልተደሰተም፤  በመሆኑም ቀጥቷቸዋል።—ዘኁልቁ 25:1-9፤ 1 ቆሮንቶስ 10:8

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለት የልደት ቀን ግብዣዎች ይናገራል። ከእነዚህ ግብዣዎች አንዱ የታላቁን አስተማሪ የልደት ቀን ለማክበር የተደረገ ነበር?— አልነበረም። ሁለቱንም የልደት ቀኖች ያከበሩት ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎች ነበሩ። አንዱ ንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ ነበር። ንጉሥ ሄሮድስ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ዘመን የገሊላ አውራጃ ገዥ ነበር።

ንጉሥ ሄሮድስ ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠርቷል። ሄሮድያዳ የተባለችውን የወንድሙን ሚስት ለራሱ ወስዶ ነበር። የአምላክ አገልጋይ የነበረው አጥማቂው ዮሐንስ፣ ሄሮድስ የወንድሙን ሚስት መውሰዱ ትክክል እንዳልሆነ ነገረው። ሄሮድስ ግን ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መናገሩ አላስደሰተውም። ስለዚህ ዮሐንስን አሳሰረው።—ሉቃስ 3:19, 20

ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ የሄሮድስ ልደት የሚከበርበት ቀን ደረሰ። በመሆኑም ሄሮድስ ትልቅ ግብዣ አዘጋጀ። በዚህ ግብዣ ላይ እንዲገኙ ብዙ ታዋቂ ሰዎችን ጠራ። ሁሉም በልተውና ጠጥተው ደስ ብሏቸው ነበር። ከዚያም የሄሮድያዳ ሴት ልጅ መጣችና ጨፈረችላቸው። ሁሉም ሰው በጭፈራዋ በመደሰቱ ንጉሥ ሄሮድስ አንድ ልዩ ስጦታ ሊሰጣት ፈለገ። “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል ቃል ገባላት።

 ታዲያ ምን ትጠይቅ ይሆን? ገንዘብ፣ የሚያማምሩ ልብሶች ወይም ደግሞ የራሷ ቤተ መንግሥት እንዲሰጣት ትጠይቅ ይሆን? ልጅቷ ምን እንደምትጠይቅ ግራ ስለገባት ወደ እናቷ ወደ ሄሮድያዳ ሄዳ “ምን ብጠይቀው ይሻላል?” አለቻት።

ሄሮድያዳ መጥምቁ ዮሐንስን በጣም ትጠላው ነበር። ስለዚህ ልጅዋ ‘የዮሐንስ ራስ ይሰጠኝ’ ብላ እንድትጠይቅ ነገረቻት። ልጅቷም ወደ ንጉሡ ተመልሳ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁኑኑ በሳህን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው።

ንጉሥ ሄሮድስ ዮሐንስ ጥሩ ሰው መሆኑን ስለሚያውቅ ሊገድለው አልፈለገም ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሡ ቃል ስለገባና ‘ሐሳቤን ብለውጥ በግብዣው ላይ የተገኙት ሰዎች ምን ይሉኛል’ ብሎ ስለፈራ ወደ እስር ቤት ሰው ልኮ የዮሐንስን ራስ አስቆረጠ። የተላከውም ሰው ወዲያውኑ ተመልሶ መጣ። የዮሐንስንም ራስ በሳህን ላይ አድርጎ ለልጅቷ ሰጣት። ከዚያም ልጅቷ ለእናቷ ሰጠቻት።—ማርቆስ 6:17-29

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ሌላው የልደት ቀን ግብዣም ቢሆን ከዚህ የተሻለ አልነበረም። ግብዣው የተደረገው የግብፁን ንጉሥ የልደት ቀን ለማክበር ነው። በዚህ ግብዣ ላይም ንጉሡ የአንድ ሰው ራስ እንዲቆረጥ አድርጓል። ከዚያም የሰውየውን ሬሳ ወፎች እንዲበሉት እንጨት  ላይ ሰቀለው! (ዘፍጥረት 40:19-22) እነዚህ ሁለት ግብዣዎች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያላቸው ይመስልሃል?— አንተ በእነዚህ ግብዣዎች ላይ መገኘት ትፈልግ ነበር?—

በሄሮድስ የልደት ቀን በተደረገው ግብዣ ላይ ምን ተፈጸመ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው ነገር ሁሉ አለምክንያት አልተጻፈም። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱት የልደት ቀን ግብዣዎች እነዚህ ብቻ ናቸው። በሁለቱም የልደት ቀኖች የአከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ ደግሞ መጥፎ ነገር ተፈጽሟል። ስለዚህ አምላክ ስለ ልደት ቀን ግብዣዎች ምን እያስተማረን ያለ ይመስልሃል? አምላክ የልደት ቀንን እንድናከብር ይፈልጋል?—

እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በልደት ቀን ግብዣዎች ላይ የሰው ራስ አይቆርጡም። ይሁን እንጂ የልደት ቀንን ማክበር የጀመሩት እውነተኛውን አምላክ የማያመልኩ ሰዎች ናቸው። አንድ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት የልደት ቀን በዓሎች ሲናገር “በተወለዱበት ቀን ትልልቅ ግብዣዎች የሚያዘጋጁት . . . ኃጢአተኞች ብቻ” እንደነበሩ ይገልጻል። (ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ) ታዲያ እኛ እንደነሱ መሆን እንፈልጋለን?—

ታላቁ አስተማሪስ የልደት ቀኑን አክብሮ ነበር?— በፍጹም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበት ቀን ስለመከበሩ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። የቀድሞዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ልደቱን አላከበሩም ነበር። ከጊዜ በኋላ ሰዎች የኢየሱስን ልደት ታኅሣሥ 25 ወይም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29 ለማክበር የመረጡት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ይህ ቀን የተመረጠው “ቀደም ሲል የሮም ሰዎች ይህን ቀን የሳተርን በዓል ብለው በመጥራት የፀሐይን ልደት ያከብሩ ስለነበረ ነው።” (ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ) ስለዚህ ሰዎች የኢየሱስን የልደት ቀን ለማክበር የመረጡት ቀደም ሲል አረማውያን በዓል ያከብሩበት በነበረ ቀን ነው!

ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ወር ሊሆን የማይችለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኢየሱስ ሲወለድ እረኞች ውጪ አድረው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚናገር ነው። (ሉቃስ 2:8-12) ኢየሱስ በተወለደበት አካባቢ ደግሞ የታኅሣሥ ወር ቀዝቃዛና ዝናባማ ስለሆነ እረኞች በዚያ ወቅት ውጪ ሊያድሩ አይችሉም።

ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 25 ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?

 ብዙ ሰዎች የገና በዓል ኢየሱስ የተወለደበት ቀን እንዳልሆነ ያውቃሉ። እንዲያውም በዚያ ቀን አረማውያን አምላክን የማያስደስት በዓል ያከብሩ እንደነበረ ያውቃሉ። ያም ሆኖ ግን ብዙ ሰዎች ገናን ያከብራሉ። እነዚህ ሰዎች የሚያሳስባቸው በዓል ማክበራቸው ነው እንጂ አምላክ ስለ በዓሉ ምን ይሰማዋል የሚለው ነገር ግድ አይሰጣቸውም። እኛ ግን ይሖዋን ማስደሰት እንፈልጋለን፣ አይደል?—

ስለዚህ ግብዣ ስናዘጋጅ ግብዣው ይሖዋን የሚያስደስት ስለ መሆኑ እርግጠኞች መሆን ያስፈልገናል። በዓመት ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ግብዣ ልናዘጋጅ እንችላለን። ግብዣ ለማዘጋጀት አንድ ልዩ ቀን መጠበቅ አያስፈልገንም። ለየት ያለ ምግብ ልንመገብና የተለያዩ ጨዋታዎችን በመጫወት ልንደሰት እንችላለን። እንዲህ ማድረግ ትፈልጋለህ?— ምናልባት ከወላጆችህ ጋር ተነጋግረህ በእነሱ እርዳታ ግብዣ ልታዘጋጅ ትችል ይሆናል። እንዲህ ማድረግ ብትችል ጥሩ ነው፣ አይደል?— ይሁን እንጂ ግብዣ ለማዘጋጀት በምታስብበት ጊዜ ግብዣው አምላክን የሚያስደስት እንዲሆን ጥረት ማድረግ አለብህ።

የምናዘጋጃቸው ግብዣዎች አምላክን የሚያስደስቱ እንዲሆኑ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ምንጊዜም በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው ነገር ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ምሳሌ 12:2፤ ዮሐንስ 8:29፤ ሮም 12:2 እና 1 ዮሐንስ 3:22 ላይም ተገልጿል።