በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 56

ኢዮስያስ የአምላክን ሕግ ይወድ ነበር

ኢዮስያስ የአምላክን ሕግ ይወድ ነበር

ኢዮስያስ የስምንት ዓመት ልጅ ሳለ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። በዚያ ዘመን ሕዝቡ የአስማት ድርጊቶች ይፈጽምና ጣዖት ያመልክ ነበር። ኢዮስያስ 16 ዓመት ሲሆነው ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ ለማምለክ ጥረት ማድረግ ጀመረ። በ20 ዓመቱ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን ጣዖታትና መሠዊያዎች ማጥፋት ጀመረ። ኢዮስያስ 26 ዓመት ሲሆነው የይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲታደስ አደረገ።

ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የይሖዋን ሕግ መጽሐፍ አገኘ፤ ምናልባትም ይህ መጽሐፍ ሙሴ ራሱ የጻፈው ሊሆን ይችላል። የንጉሡ ጸሐፊ የሆነው ሳፋን መጽሐፉን ወደ ኢዮስያስ አምጥቶ ሕጉን ጮክ ብሎ አነበበለት። ኢዮስያስም የሕጉን ቃል ሲሰማ ሕዝቡ ለብዙ ዓመታት ይሖዋን እንዳልታዘዙ ተገነዘበ። ንጉሥ ኢዮስያስ ኬልቅያስን እንዲህ አለው፦ ‘ይሖዋን በጣም አስቆጥተነዋል። ሂድና ይሖዋን ጠይቅ። ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል።’ ይሖዋም በነቢዪቱ ሕልዳና አማካኝነት እንዲህ በማለት መልስ ሰጠ፦ ‘የይሁዳ ሰዎች ትተውኛል። ስለዚህ መቀጣት አለባቸው፤ የሚቀጡት ግን ኢዮስያስ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ዘመን አይደለም፤ ምክንያቱም እሱ ራሱን ዝቅ አድርጓል።’

ንጉሥ ኢዮስያስ መልእክቱን ሲሰማ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደና የይሁዳን ሕዝብ ሰበሰበ። ከዚያም የይሖዋን ሕግ ለመላው ሕዝብ ጮክ ብሎ አነበበ። ኢዮስያስና ሕዝቡም፣ በሙሉ ልባቸው ይሖዋን ለመታዘዝ ቃል ገቡ።

የይሁዳ ሰዎች የፋሲካን በዓል ካከበሩ ብዙ ዓመታት አልፈው ነበር። ሆኖም ኢዮስያስ የፋሲካ በዓል በየዓመቱ መከበር እንዳለበት በሕጉ መጽሐፍ ላይ ሲያነብ  ሕዝቡን ‘ለይሖዋ ፋሲካ እናደርጋለን’ አላቸው። ከዚያም ኢዮስያስ ብዙ መሥዋዕት አዘጋጀ፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚዘምሩ ዘማሪዎችን መደበ። ከዚያም የይሁዳ ሰዎች ፋሲካን አከበሩ፤ ቀጥሎም ለሰባት ቀን ያህል የቂጣ በዓልን አከበሩ። ከሳሙኤል ዘመን አንስቶ እንደዚህ ያለ የፋሲካ በዓል ተከብሮ አያውቅም ነበር። ኢዮስያስ በእርግጥም የአምላክን ሕግ ይወድ ነበር። አንተስ ስለ ይሖዋ መማር ያስደስትሃል?

“ቃልህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።”—መዝሙር 119:105