በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 54

ይሖዋ ዮናስን በትዕግሥት አስተማረው

ይሖዋ ዮናስን በትዕግሥት አስተማረው

የአሦር ከተማ በሆነችው በነነዌ የሚኖሩት ሰዎች በጣም ክፉዎች ነበሩ። ይሖዋ ነቢዩ ዮናስን ‘ወደ ነነዌ ሰዎች ሄደህ ክፉ ሥራችሁን ተዉ ብለህ ንገራቸው’ ብሎ አዘዘው። ዮናስ ግን ወደ ነነዌ መሄድ ሲገባው አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ተርሴስ የሚሄድ መርከብ ላይ ተሳፈረ።

መርከቡ በባሕሩ ላይ እየሄደ ሳለ ከባድ ማዕበል ስለተነሳ መርከበኞቹ በጣም ፈሩ። በመሆኑም ‘ይህ የደረሰብን ለምንድን ነው?’ ብለው ወደ አምላኮቻቸው ጸለዩ። በመጨረሻም ዮናስ እንዲህ አላቸው፦ ‘ይህ የደረሰባችሁ በእኔ ምክንያት ነው። እኔ ይሖዋ ያዘዘኝን ነገር ትቼ ወደ ሌላ ቦታ እየሄድኩ ነው። እኔን ወደ ባሕሩ ከጣላችሁኝ ማዕበሉ ይቆማል።’ መርከበኞቹ ዮናስን ሊጥሉት አልፈለጉም፤ ዮናስ ግን እንዲጥሉት በተደጋጋሚ ነገራቸው። ከዚያም ዮናስን ወደ ባሕሩ ሲወረውሩት ማዕበሉ ቆመ።

ዮናስ የሚሞት መስሎት ነበር። ባሕሩ ውስጥ እየሰመጠ ሲሄድ ወደ ይሖዋ ጸለየ። ይሖዋም አንድ ትልቅ ዓሣ ላከለት። ዓሣው ዮናስን ዋጠው፤ ዮናስ ግን አልሞተም። ዮናስ በዓሣው ውስጥ ሆኖ ‘ከዚህ በኋላ ሁልጊዜ አንተን እታዘዛለሁ’ በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። ይሖዋም ዮናስን ለሦስት ቀናት ዓሣው ውስጥ አቆየው፤ ከዚያም ዓሣው ዮናስን ደረቅ ምድር ላይ እንዲተፋው አደረገ።

ዮናስ ከባሕሩ ከወጣ በኋላ ይሖዋ ወደ ነነዌ እንዲሄድ በድጋሚ አዘዘው። በዚህ ጊዜ ግን ዮናስ የተባለውን አደረገ። ወደ ነነዌ ሄዶ እነዚያን ክፉ ሰዎች ‘ነነዌ በ40 ቀን ውስጥ ትጠፋለች’ አላቸው። ከዚያም አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፤ የነነዌ ሰዎች የዮናስን መልእክት ሰምተው ክፉ ነገር መሥራት አቆሙ። የነነዌ  ንጉሥ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ ‘ወደ አምላክ ጸልዩ፤ ንስሐም ግቡ። ምናልባት ምሕረት ያደርግልን ይሆናል።’ ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ንስሐ መግባታቸውን ሲያይ ነነዌን ሳያጠፋት ቀረ።

ዮናስ ከተማዋ ስላልጠፋች በጣም ተበሳጨ። እስቲ አስበው፦ ይሖዋ ለዮናስ ትዕግሥትና ምሕረት አሳይቶታል፤ ዮናስ ግን የነነዌ ሰዎች ምሕረት እንዲደረግላቸው አልፈለገም። በመሆኑም ከከተማዋ ወጣና በአንዲት የቅል ተክል ጥላ ሥር አኩርፎ ተቀመጠ። ከዚያም የቅል ተክሏ ደረቀች፤ በዚህ ጊዜ ዮናስ በጣም ተናደደ። ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ይህች ተክል ስለደረቀች አዘንክ። እኔስ በነነዌ ለሚኖሩ ሰዎች ማዘን የለብኝም? ንስሐ ስለገቡ አላጠፋኋቸውም።’ ይሖዋ ዮናስን ሊያስተምረው የፈለገው ነገር ምን ነበር? በነነዌ የሚኖሩ ሰዎች ሕይወት ከየትኛውም ተክል የበለጠ ዋጋ እንዳለው ሊያስተምረው ፈልጎ ነበር።

“ይሖዋ . . . እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።”—2 ጴጥሮስ 3:9