ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት ንጉሥ ሆነ። በወቅቱ ዳዊት 30 ዓመቱ ነበር። ለተወሰኑ ዓመታት ንጉሥ ሆኖ ከገዛ በኋላ አንድ ከባድ ስህተት ሠራ። አንድ ቀን ምሽት ላይ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት አየ። ዳዊት ስለ ሴትየዋ ማንነት ሲጠይቅ ስሟ ቤርሳቤህ እንደሆነና ኦርዮ የሚባል አንድ ወታደር ሚስት እንደሆነች ነገሩት። ዳዊት ቤርሳቤህን ወደ ቤተ መንግሥቱ አስመጣት። ከዚያም አብሯት ተኛ፤ እሷም አረገዘች። ዳዊት ያደረገውን ነገር ለመደበቅ ሞከረ። ለጦር አዛዡ መልእክት ልኮ ኦርዮን ውጊያው ላይ ፊት ለፊት እንዲያሰልፈውና ሌሎቹ ወታደሮች ጥለውት እንዲሸሹ እንዲያደርግ ነገረው። ኦርዮ በጦርነቱ ከተገደለ በኋላ ዳዊት ቤርሳቤህን አገባት።

ሆኖም ይሖዋ የተፈጸመውን መጥፎ ድርጊት በሙሉ ተመልክቶ ነበር። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ይሖዋ ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው። ናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘አንድ ሀብታም ሰውና አንድ ድሃ ሰው ነበሩ፤ ሀብታሙ ሰው ብዙ በጎች ነበሩት፤ ድሃው ግን የነበረችው አንዲት ትንሽ የበግ ጠቦት ብቻ ነበረች። እሷንም በጣም ይወዳት ነበር። ሀብታሙ ሰው ድሃው የነበረችውን አንዲት ጠቦት ወሰደበት።’ በዚህ ጊዜ ዳዊት በጣም ተናዶ ‘ያ ሀብታም ሰው መሞት ይገባዋል!’ አለ። ከዚያም ናታን ዳዊትን ‘ያ ሀብታም ሰው አንተ ነህ!’ አለው። ዳዊት በጣም አዘነ፤ ከዚያም ጥፋቱን በማመን ‘በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ’ አለ። ይህ ኃጢአት በዳዊትና በቤተሰቡ ላይ ብዙ ችግር አምጥቷል። ይሖዋ ዳዊትን የቀጣው ቢሆንም ዳዊት ሐቀኛና ትሑት በመሆኑ በሕይወት እንዲኖር ፈቅዶለታል።

ዳዊት ለይሖዋ ቤተ መቅደስ መገንባት ፈልጎ ነበር፤ ይሖዋ ግን ቤተ መቅደሱን እንዲገነባ የመረጠው ልጁን ሰለሞንን ነበር። ዳዊት ቤተ መቅደሱን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለሰለሞን ማዘጋጀት ጀመረ፤ እንዲህም አለ፦ ‘የይሖዋ  ቤተ መቅደስ በጣም ውብ መሆን አለበት። ሰለሞን ገና ልጅ ነው፤ ስለዚህ የሚያስፈልገውን ነገር በማዘጋጀት እረዳዋለሁ።’ ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚሆን በጣም ብዙ ገንዘብ ሰጠ። እንዲሁም ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞችን አዘጋጀለት። ወርቅና ብር አሰባሰበ፤ ከጢሮስና ከሲዶናም የአርዘ ሊባኖስ እንጨት አስመጣ። ዳዊት መሞቻው ሲቃረብ ለሰለሞን ቤተ መቅደሱ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ንድፍ ሰጠው። እንዲህም አለው፦ ‘ይሖዋ እነዚህን ነገሮች በጽሑፍ እንዳሰፍርልህ ነግሮኛል። ይሖዋ ይረዳሃል። አትፍራ። ደፋር ሁን፤ ሥራውን በትጋት አከናውን።’

“የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ሁሉ ግን ምሕረት ያገኛል።”—ምሳሌ 28:13