በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 32

አዲሱ መሪና ሁለቱ ደፋር ሴቶች

አዲሱ መሪና ሁለቱ ደፋር ሴቶች

ኢያሱ ለብዙ ዓመታት የይሖዋን ሕዝቦች ሲመራ ከቆየ በኋላ በ110 ዓመቱ ሞተ። እሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን ይሖዋን ያመልኩ ነበር። ኢያሱ ከሞተ በኋላ ግን ልክ እንደ ከነአናውያን ጣዖት ማምለክ ጀመሩ። እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸው ይሖዋ ያቢን የተባለ የከነአን ንጉሥ እንዲያሠቃያቸው ፈቀደ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ስለዚህ ይሖዋ፣ ባርቅ የተባለ አዲስ መሪ ሾመላቸው። ባርቅ ሕዝቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ የመርዳት ኃላፊነት ነበረበት።

ነቢይቷ ዲቦራ ባርቅን አስጠራችው። ከዚያም ይሖዋ የላከለትን የሚከተለውን መልእክት ነገረችው፦ ‘10,000 ወንዶች ይዘህ ወደ ቂሾን ወንዝ ሂድና ከያቢን ሠራዊት ጋር ተዋጋ። የያቢን ሠራዊት አለቃ የሆነውን ሲሳራን ታሸንፈዋለህ።’ ባርቅም ዲቦራን ‘እኔ የምሄደው አንቺ አብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ ብቻ ነው’ አላት። እሷም እንዲህ አለችው፦ ‘አብሬህ እሄዳለሁ። ግን ሲሳራን የምትገድለው አንተ እንደማትሆን እወቅ። ይሖዋ፣ ሲሳራን የምትገድለው አንዲት ሴት እንደሆነች ተናግሯል።’

ዲቦራ ከባርቅና ከሠራዊቱ ጋር እስከ ታቦር ተራራ ድረስ አብራ ሄደች፤ በዚያም ለውጊያ ተዘጋጁ። ሲሳራ ይህን እንደሰማ የጦር ሠረገሎቹንና ሠራዊቱን ከታቦር ተራራ ሥር ባለው ሸለቆ ሰበሰበ። ዲቦራም ባርቅን ‘ዛሬ ይሖዋ እንድታሸንፍ ይረዳሃል’ አለችው። ባርቅና 10,000 ወታደሮቹ ኃይለኛ ከሆነው የሲሳራ ሠራዊት ጋር ለመጋጠም ከተራራው ወረዱ።

 ከዚያም ይሖዋ የቂሾን ወንዝ ሞልቶ አካባቢውን እንዲያጥለቀልቅ አደረገ። የሲሳራ የጦር ሠረገሎች ጭቃ ስለያዛቸው መሄድ አልቻሉም። ሲሳራ ከሠረገላው ላይ ወርዶ መሸሽ ጀመረ። ባርቅና ወታደሮቹ የሲሳራን ሠራዊት አሸነፉ፤ ሲሳራ ግን አመለጠ! ሲሳራ ሸሽቶ ኢያዔል የምትባል ሴት ድንኳን ውስጥ ተደበቀ። እሷም የሚጠጣው ወተት ሰጠችውና ብርድ ልብስ አለበሰችው። ሲሳራ ደክሞት ስለነበር እንቅልፍ ወሰደው። ከዚያም ኢያዔል በቀስታ ወደ እሱ ተጠግታ ጭንቅላቱ ላይ የድንኳን ካስማ ሰካችበት። በዚህ ሁኔታ ሲሳራ ሞተ።

ባርቅ ሲሳራን ፍለጋ መጣ። ኢያዔልም ከድንኳኗ ወጥታ ‘ና፣ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ’ አለችው። ባርቅ ወደ ውስጥ ሲገባ ሲሳራን ሞቶ አገኘው። ባርቅና ዲቦራም፣ ይሖዋ ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉ ስለረዳቸው በመዝሙር አወደሱት። ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በሰላም ኖሩ።

“ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው።”—መዝሙር 68:11