በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 35

ሐና ልጅ ለማግኘት ጸለየች

ሐና ልጅ ለማግኘት ጸለየች

ሕልቃና የሚባል አንድ እስራኤላዊ ሐና እና ፍናና የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ሆኖም ሕልቃና አስበልጦ የሚወደው ሐናን ነበር። ፍናና ብዙ ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም፤ ስለዚህ ፍናና ሁልጊዜ በሐና ላይ ታሾፍባት ነበር። ሕልቃና በሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን ይሖዋን ለማምለክ በየዓመቱ ቤተሰቡን ይዞ ይሄድ ነበር። በአንድ ወቅት ወደ ሴሎ ሄደው ሳለ ሕልቃና የሚወዳት ሚስቱ ሐና በጣም እንዳዘነች አስተዋለ። ስለዚህ ‘ሐና፣ እባክሽ አታልቅሺ። እኔ አለሁልሽ። እኔ እኮ በጣም ነው የምወድሽ’ አላት።

በኋላም ሐና ብቻዋን ሆና ለመጸለይ ሄደች። ይሖዋን እንዲረዳት እያለቀሰች ለመነችው። እንዲህ በማለት ቃል ገባች፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ ወንድ ልጅ ብትሰጠኝ ለአንተ እሰጠዋለሁ፤ እሱም ዕድሜውን ሙሉ ያገለግልሃል።’

ሊቀ ካህናቱ ኤሊ፣ ሐና እያለቀሰች ስትጸልይ ሲያይ የሰከረች መሰለው። ሐናም እንዲህ አለችው፦ ‘ሰክሬ አይደለም ጌታዬ። ከባድ ችግር ስላለብኝ ይሖዋ እንዲረዳኝ እየለመንኩት ነው።’ ኤሊም እንደተሳሳተ ሲገባው ‘አምላክ የምትፈልጊውን ነገር ይስጥሽ’ አላት። ሐናም ተጽናንታ ሄደች። ከዚያም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳሙኤል አለችው። ሐና ልጅ በማግኘቷ ምን ያህል ተደስታ ሊሆን እንደሚችል አስበው።

ሐና ለይሖዋ የገባችውን ቃል አልረሳችም። ልክ ሳሙኤል ጡት መጥባት እንዳቆመ ወደ  ማደሪያ ድንኳኑ አመጣችው። ከዚያም ኤሊን እንዲህ አለችው፦ ‘ስጸልይ የነበረው ይህን ልጅ ለማግኘት ነበር። በሕይወቱ ሙሉ ይሖዋን እንዲያገለግል ለእሱ እሰጠዋለሁ።’ ሕልቃናና ሐና በየዓመቱ ሳሙኤልን ለመጠየቅ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ሲሄዱ አዲስ ልብስ ያመጡለት ነበር። ይሖዋ ከዚያ በኋላ ለሐና ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች ሰጣት።

“ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ።”—ማቴዎስ 7:7