በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 37

ይሖዋ ሳሙኤልን አነጋገረው

ይሖዋ ሳሙኤልን አነጋገረው

ሊቀ ካህናቱ ኤሊ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ካህናት ሆነው የሚያገለግሉ ሆፍኒ እና ፊንሃስ የሚባሉ ሁለት ልጆች ነበሩት። ሆፍኒ እና ፊንሃስ የይሖዋን ሕግ አይታዘዙም ነበር፤ እንዲሁም በሕዝቡ ላይ በደል ይፈጽሙ ነበር። እስራኤላውያን ለይሖዋ መሥዋዕት ይዘው ሲመጡ ሆፍኒ እና ፊንሃስ ምርጥ የሆነውን ሥጋ ለራሳቸው ይወስዱ ነበር። ኤሊ ልጆቹ የሚያደርጉትን ነገር ቢሰማም ምንም እርምጃ አልወሰደም። ታዲያ ይሖዋ ዝም ብሎ ይመለከታቸው ይሆን?

ሳሙኤል ዕድሜው ከሆፍኒ እና ከፊንሃስ በጣም የሚያንስ ቢሆንም የእነሱን ምሳሌ አልተከተለም። ይሖዋ በሳሙኤል ተደስቶ ነበር። አንድ ቀን ሳሙኤል ተኝቶ ሳለ አንድ ድምፅ ሲጠራው ሰማ። ሳሙኤልም ተነስቶ ወደ ኤሊ እየሮጠ ሄደና ‘አቤት፣ ጠራኸኝ?’ አለው። ኤሊ ግን ‘አይ አልጠራሁህም። ተመልሰህ ተኛ’ አለው። ሳሙኤልም ተመልሶ ተኛ። ከዚያም በድጋሚ ያንን ድምፅ ሰማና ወደ ኤሊ ሄደ፤ ሆኖም በዚህ ጊዜም ኤሊ አልጠራውም ነበር። ሳሙኤል ለሦስተኛ ጊዜ ያንን ድምፅ ሲሰማ፣ ኤሊ ሳሙኤልን እየጠራው ያለው ይሖዋ እንደሆነ ተገነዘበ። ስለዚህ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘ድጋሚ ያንን ድምፅ ከሰማህ “ይሖዋ ሆይ፣ እኔ አገልጋይህ እየሰማሁ ስለሆነ ተናገር” በለው።’

ሳሙኤል ተመልሶ ተኛ። ከዚያም ‘ሳሙኤል! ሳሙኤል!’ የሚል ድምፅ ሰማ። ሳሙኤልም ‘እኔ አገልጋይህ እየሰማሁ ስለሆነ ተናገር’ አለ። ይሖዋም እንዲህ አለው፦ ‘ኤሊንና ቤተሰቡን ልቀጣ እንደሆነ ለኤሊ ንገረው። ኤሊ ልጆቹ  በማደሪያ ድንኳኔ ውስጥ መጥፎ ነገር እንደሚያደርጉ እያወቀ ምንም እርምጃ አልወሰደም።’ በቀጣዩ ቀን ጠዋት ሳሙኤል እንደተለመደው የማደሪያውን ድንኳን በሮች ከፈተ። ይሖዋ የነገረውን ነገር ለሊቀ ካህናቱ ለመናገር ፈርቶ ነበር። ኤሊ ግን ጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ፣ ይሖዋ የነገረህ መልእክት ምንድን ነው? ሁሉንም ነገር ንገረኝ።’ ስለሆነም ሳሙኤል ለኤሊ ሁሉንም ነገር ነገረው።

ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ ይሖዋ ምንጊዜም ከሳሙኤል ጋር ሆኖ ይረዳው ነበር። በሁሉም ቦታ የሚገኙ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ሳሙኤልን ነቢይና ፈራጅ አድርጎ እንደመረጠው አወቁ።

“በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ።”—መክብብ 12:1