በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ትምህርት 38

ይሖዋ ለሳምሶን ታላቅ ኃይል ሰጠው

ይሖዋ ለሳምሶን ታላቅ ኃይል ሰጠው

ከእስራኤላውያን መካከል አብዛኞቹ በድጋሚ ጣዖት ማምለክ ጀመሩ፤ ስለዚህ ይሖዋ ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን እንዲያሠቃዩአቸው ፈቀደ። ነገር ግን ይሖዋን የሚወዱ ጥቂት እስራኤላውያን ነበሩ። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ማኑሄ ነበር። ማኑሄና ሚስቱ ልጅ አልነበራቸውም። አንድ ቀን ይሖዋ የላከው መልአክ ወደ ማኑሄ ሚስት መጥቶ አነጋገራት፤ እንዲህም አላት፦ ‘ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። እሱም እስራኤልን ከፍልስጤማውያን ነፃ ያወጣል፤ እንዲሁም ናዝራዊ ይሆናል።’ ናዝራውያን የሚባሉት እነማን እንደሆኑ ታውቃለህ? ናዝራውያን ለየት ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ነበሩ። ይሖዋ ያወጣው ሕግ እነዚህ ሰዎች ፀጉራቸውን እንዳይቆረጡ ያዝዝ ነበር።

ከጊዜ በኋላ የማኑሄ ልጅ ተወለደ፤ ስሙም ሳምሶን ተባለ። ሳምሶን ሲያድግ ይሖዋ ኃይል ስለሰጠው በጣም ጠንካራ ሰው ሆነ። ያለምንም መሣሪያ አንበሳ መግደል ይችል ነበር። በአንድ ወቅት ሳምሶን ብቻውን 30 ፍልስጤማውያንን ገድሏል። ፍልስጤማውያን ሳምሶንን ይጠሉት ስለነበር ሊገድሉት አሰቡ። አንድ ቀን ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄዶ እዚያ አደረ፤ በዚህ ወቅት ፍልስጤማውያን ጠዋት ላይ ሊገድሉት ስለፈለጉ ወደ ከተማዋ በር ሄደው ሳምሶንን መጠበቅ ጀመሩ። ሳምሶን ግን በሌሊት ተነስቶ ወደ ከተማዋ መግቢያ ሄደና በሩን ከአጥሩ ላይ ነቀለው። ከዚያም በሩን በትከሻው ተሸክሞ በኬብሮን አካባቢ እስከሚገኘው ተራራ አናት ድረስ ይዞት ሄደ!

በኋላም ፍልስጤማውያን ደሊላ ወደምትባል የሳምሶን ጓደኛ ሄደው እንዲህ አሏት፦ ‘ሳምሶን እንዲህ ጠንካራ የሆነው ለምን እንደሆነ ከነገርሽን በጣም ብዙ ገንዘብ እንሰጥሻለን። ሳምሶንን ይዘን እስር ቤት ልናስገባው እንፈልጋለን።’ ደሊላም ገንዘቡን ማግኘት ስለፈለገች በሐሳባቸው ተስማማች። መጀመሪያ ላይ ሳምሶን፣ ይህን ያህል ጠንካራ ሊሆን የቻለው ለምን እንደሆነ ሊነግራት አልፈለገም ነበር። እሷ ግን በጣም ስለጨቀጨቀችው ሚስጥሩን ነገራት። እንዲህ አላት፦ ‘ናዝራዊ ስለሆንኩ ፀጉሬ ተቆርጦ አያውቅም። ፀጉሬ ከተቆረጠ ግን ኃይሌን አጣለሁ።’ ሳምሶን ይህን ለእሷ መናገሩ ትልቅ ስህተት ነበር።

ደሊላ ወዲያውኑ ፍልስጤማውያንን ‘ሚስጥሩን አውቄያለሁ!’ አለቻቸው። ሳምሶንን እግሯ ላይ አስተኛችውና ሰው ጠርታ ፀጉሩን አስቆረጠችው። ከዚያም ‘ሳምሶን፣ ፍልስጤማውያን መጡብህ!’ ብላ ጮኸች። ሳምሶን ከእንቅልፉ ሲነቃ  ምንም ኃይል አልነበረውም። በመሆኑም ፍልስጤማውያን ያዙትና ዓይኖቹን አውጥተው እስር ቤት አስገቡት።

አንድ ቀን በሺህ የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በአምላካቸው በዳጎን ቤተ መቅደስ ተሰብስበው እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር፦ ‘አምላካችን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል! ሳምሶንን አምጡትና እንጫወትበት።’ ከዚያም ሳምሶንን በሁለት ምሰሶዎች መሃል አቁመው ያሾፉበት ጀመር። ሳምሶንም ‘ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ አንድ ጊዜ ብቻ ኃይል ስጠኝ’ በማለት ጸለየ። በዚህ ወቅት የሳምሶን ፀጉር እንደገና አድጎ ነበር። ሳምሶን ባለ በሌለ ኃይሉ የቤተ መቅደሱን ምሰሶዎች ገፋቸው። ከዚያም ሕንፃው በሙሉ ፈራረሰና በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙሉ ገደላቸው፤ ሳምሶንም ሞተ።

“ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13