ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ። ሕጎቼን በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፌ እሰጥሃለሁ።’ ሙሴ ወደ ተራራው ወጣና በዚያ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ። ሙሴ እዚያ በቆየበት ጊዜ ውስጥ ይሖዋ አሥርቱን ትእዛዛት በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠው።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ሙሴ ትቷቸው የሄደ መሰላቸው። ስለዚህ አሮንን ‘መሪ ያስፈልገናል። አምላክ ሥራልን!’ አሉት። አሮንም ‘ወርቃችሁን ስጡኝ’ አላቸው። ከዚያም ወርቁን አቅልጦ የጥጃ ሐውልት ሠራ። ሰዎቹም ‘ከግብፅ መርቶ ያወጣን አምላካችን ይህ ጥጃ ነው!’ አሉ። በመሆኑም የወርቁን ጥጃ ማምለክ ጀመሩ፤ እንዲሁም ትልቅ ድግስ አዘጋጁ። ይህን ማድረጋቸው ስህተት ነበር? አዎ፣ ምክንያቱም ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ቃል ገብተው ነበር። አሁን ግን ይህን ቃላቸውን አልጠበቁም።

ይሖዋ እስራኤላውያን ያደረጉትን ነገር አየና ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ ሕዝቡ ሂድ። እኔን አልታዘዙም፤ የሐሰት አምላክ እያመለኩ ነው።’ በመሆኑም ሙሴ ሁለቱን ጽላቶች ይዞ ከተራራው ወረደ።

 ሙሴ ወደ ሰፈሩ ሲጠጋ እስራኤላውያን ሲዘምሩ ሰማ። ከዚያም ሲጨፍሩና ለጥጃው ሲሰግዱ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ ሙሴ በጣም ተናደደ። ጽላቶቹን ወደ መሬት ሲወረውራቸው ተሰባበሩ። የጥጃውንም ሐውልት ወዲያውኑ ወስዶ አቃጠለው። ከዚያም አሮንን ‘እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ልታደርግ የቻልከው ሕዝቡ ምን ብሎ ቢያሳምንህ ነው?’ ብሎ ጠየቀው። አሮንም እንዲህ አለ፦ ‘እባክህ አትቆጣ። እነሱ እንደሆነ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ታውቃለህ። አምላክ ሥራልን አሉኝ፤ ስለዚህ ወርቃቸውን እሳቱ ውስጥ ጣልኩት፤ ከዚያ ይህ ጥጃ ወጣ!’ አሮን እንዲህ ማድረግ አልነበረበትም። ሙሴ ተመልሶ ወደ ተራራው በመውጣት ሕዝቡን ይቅር እንዲል ይሖዋን ለመነው።

ይሖዋ እሱን ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ይቅር አላቸው። እስራኤላውያን የሙሴን አመራር መከተላቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር አስተዋልክ?

“ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤ እሱ በሞኞች አይደሰትምና። ስእለትህን ፈጽም።”—መክብብ 5:4