በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 23

እስራኤላውያን ለይሖዋ ቃል ገቡ

እስራኤላውያን ለይሖዋ ቃል ገቡ

እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ ወደ ሲና ተራራ ደረሱ፤ በዚያም ድንኳናቸውን ተከሉ። ሙሴ ወደ ተራራው ከወጣ በኋላ ይሖዋ ጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘እስራኤላውያንን ያዳንኳቸው እኔ ነኝ። ከታዘዙኝና ሕጎቼን ከጠበቁ ለእኔ ልዩ ሕዝብ ይሆናሉ።’ ከዚያም ሙሴ ተመልሶ ወረደና ይሖዋ ያለውን ነገር ለእስራኤላውያን ነገራቸው። እነሱም ‘ይሖዋ አድርጉ ያለንን ነገር በሙሉ እናደርጋለን’ ሲሉ መለሱ።

ሙሴ ተመልሶ ወደ ተራራው ወጣ። ይሖዋም እንዲህ አለው፦ ‘በሦስት ቀን ውስጥ አነጋግርሃለሁ። ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ ለመውጣት እንዳይሞክሩ አስጠንቅቃቸው።’ ሙሴ ከተራራው ወረደና እስራኤላውያንን ‘የይሖዋን ቃል ለመስማት ተዘጋጁ’ አላቸው።

በሦስተኛው ቀን፣ እስራኤላውያን ተራራው ላይ መብረቅና ጥቁር ደመና አዩ። የነጎድጓድና የቀንደ መለከት ድምፅም ሰሙ። ከዚያም ይሖዋ ወደ ተራራው በእሳት ወረደ። እስራኤላውያን በጣም ከመፍራታቸው የተነሳ ተንቀጠቀጡ። መላው ተራራ በኃይል ተናወጠ፤ እንዲሁም በጭስ ተሞላ። የቀንደ መለከቱ ድምፅም ይበልጥ እየጨመረ መጣ። ከዚያም አምላክ እንዲህ አለ፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን ማምለክ የለባችሁም።’

ሙሴ ተመልሶ ወደ ተራራው ወጣ፤ ይሖዋም ሕዝቡ እንዴት ሊያመልኩት እንደሚገባ እንዲሁም ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ነገሮች የሚገልጽ ሕግ ሰጠው። ሙሴ ሕጉን ጻፈና ለእስራኤላውያን አነበበላቸው። እነሱም ‘ይሖዋ እንድናደርግ ያዘዘንን ነገር በሙሉ እናደርጋለን’ በማለት ለአምላክ ቃል ገቡ። ታዲያ ቃላቸውን ይጠብቁ ይሆን?

“አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።”—ማቴዎስ 22:37