በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 19

የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች

የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች

ግብፃውያን እስራኤላውያንን ባሪያ አድርገዋቸው ስለነበር የጉልበት ሥራ ያሠሯቸው ነበር። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ወደ ፈርዖን በመላክ ‘“ወደ ምድረ በዳ ሄደው እንዲያመልኩኝ ሕዝቤን ልቀቅ” ብላችሁ ንገሩት’ አላቸው። ፈርዖን ‘ይሖዋ የፈለገውን ቢል ግድ አይሰጠኝም፤ እስራኤላውያንን አለቅም’ በማለት በትዕቢት መለሰ። ከዚያም ፈርዖን የእስራኤላውያንን ሥራ የባሰ አከበደባቸው። ይሖዋ ግን ፈርዖንን አንድ ትልቅ ትምህርት ሊያስተምረው ነው። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? በግብፅ ላይ አሥር መቅሰፍቶች በማምጣት ነው። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ፈርዖን የእኔን ትእዛዝ አልሰማም። ጠዋት ላይ ወደ አባይ ወንዝ ይሄዳል። ስለዚህ ወደ እሱ ሂድና “ሕዝቤን አለቅም ስላልክ አባይ ውስጥ ያለው ውኃ በሙሉ ወደ ደም ይቀየራል” በለው።’ ሙሴ ይሖዋን በመታዘዝ ወደ ፈርዖን ሄደ። ፈርዖን እያየ አሮን የአባይን ወንዝ በዱላው ሲመታው ወንዙ ወደ ደም ተቀየረ። በዚህ ጊዜ ወንዙ መሽተት ጀመረ፤ ዓሦቹም ሞቱ፤ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ከአባይ ወንዝ መጠጣት አልቻለም። ፈርዖን ግን አሁንም እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

 ከሰባት ቀን በኋላ ይሖዋ ሙሴን እንደገና ወደ ፈርዖን በመላክ እንዲህ ብሎ እንዲነግረው አዘዘው፦ ‘ሕዝቤን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆንክ የግብፅ ምድር በሙሉ በእንቁራሪት ይሞላል።’ አሮንም ዱላውን አነሳ። ከዚያም እንቁራሪቶች ከውኃ እየወጡ ወደ ሰዎች ቤት ገቡ፤ ዕቃቸው ሁሉ በእንቁራሪት ተሞላ፤ አልጋቸውም ላይ ወጡ። ሁሉም ቦታ በእንቁራሪት ተሞልቶ ነበር! በዚህ ጊዜ ፈርዖን ሙሴን ‘ይህን መቅሰፍት እንዲያቆምልን ይሖዋን ለምንልን’ አለው። ፈርዖን እስራኤላውያንን እንደሚለቅ ቃል ገባ። ስለዚህ ይሖዋ መቅሰፍቱን አስቆመ፤ ግብፃውያኑም የሞቱትን እንቁራሪቶች ሰብስበው ከመሯቸው። ምድሪቱም መሽተት ጀመረች። ፈርዖን ግን አሁንም ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

ከዚያም ይሖዋ ሙሴን ‘አሮን መሬቱን በዱላው ይምታው፤ ከዚያም አቧራው ወደ ትንኝ ይቀየራል’ አለው። ወዲያውኑ ምድሩ በሙሉ በትንኝ ተወረረ። የፈርዖን አገልጋዮች ራሳቸው ፈርዖንን ‘ይህ መቅሰፍት ከአምላክ የመጣ ነው’ አሉት። ፈርዖን ግን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

“ኃይሌንና ብርታቴን እንዲያውቁ አደርጋለሁ፤ እነሱም ስሜ ይሖዋ መሆኑን ያውቃሉ።”—ኤርምያስ 16:21