ዮሴፍ፣ ያዕቆብ መጨረሻ ላይ ከወለዳቸው ልጆች መካከል አንዱ ነበር። ታላላቅ ወንድሞቹ አባታቸው ዮሴፍን ከእነሱ አስበልጦ እንደሚወደው አዩ። ይህን ሲያውቁ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል? በዮሴፍ ላይ ቅናት ስላደረባቸው ጠሉት። ዮሴፍ ሕልም አይቶ ለወንድሞቹ ነገራቸው። በሕልሙ ያየው ነገር ወንድሞቹ አንድ ቀን ለእሱ እንደሚሰግዱ የሚያመለክት ነበር። ይህ ደግሞ የባሰ እንዲጠሉት አደረጋቸው!

አንድ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች በሴኬም ከተማ አቅራቢያ በጎች እየጠበቁ ነበር። ያዕቆብ ‘ወንድሞችህ ደህና መሆናቸውን አይተህ ና’ ብሎ ዮሴፍን ላከው። ወንድሞቹ ዮሴፍ ሲመጣ ከሩቅ አዩትና እርስ በርሳቸው ‘ያ ሕልም አላሚ መጣ። ኑ እንግደለው!’ ተባባሉ። ከዚያም ያዙትና ወደ አንድ ጥልቅ ጉድጓድ ወረወሩት። ከወንድሞቹ አንዱ የሆነው ይሁዳ ግን ‘አትግደሉት! ባሪያ አድርገን ብንሸጠው ይሻላል’ አለ። ስለዚህ ዮሴፍን ወደ ግብፅ ለሚሄዱ ምድያማውያን ነጋዴዎች በ20 የብር ሰቅል ሸጡት።

ከዚያም የዮሴፍ ወንድሞች የዮሴፍን ልብስ የፍየል ደም ውስጥ ነከሩትና ወደ አባታቸው በመላክ ‘ይህ የልጅህ ልብስ አይደለም?’ አሉት። ስለዚህ ያዕቆብ ዮሴፍን አውሬ የበላው መሰለው። በዚህ የተነሳ በጣም አዘነ። ማንም ሊያጽናናው አልቻለም።

ዮሴፍ በግብፅ ለሚኖር ጶጢፋር የተባለ ባለሥልጣን ባሪያ ሆኖ ተሸጠ። ሆኖም ይሖዋ ዮሴፍን ይረዳው ነበር። ጶጢፋር፣ ዮሴፍ ጎበዝ ሠራተኛና እምነት የሚጣልበት ሰው እንደሆነ አየ። ስለዚህ ዮሴፍ የጶጢፋርን ንብረት ሁሉ እንዲቆጣጠር ተሾመ።

የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍ ቆንጆና ጥሩ ቁመና ያለው እንደሆነ አየች። በየቀኑ ዮሴፍን አብሯት እንዲተኛ ትጠይቀው ነበር። ዮሴፍ ምን ያደርግ ይሆን? እንዲህ አላት፦ ‘አይሆንም! ይህ ተገቢ አይደለም። ጌታዬ እኔን ያምነኛል፤ አንቺ ደግሞ ሚስቱ ነሽ። ከአንቺ ጋር ከተኛሁ በአምላክ ፊት ኃጢአት እሠራለሁ!’

 አንድ ቀን የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍን አብሯት እንዲተኛ ለማስገደድ ሞከረች። ልብሱን ጭምድድ አድርጋ ያዘችው፤ እሱ ግን ሸሽቶ አመለጠ። ጶጢፋር ወደ ቤት ሲመለስ ዮሴፍ ከእሱ ጋር እንድትተኛ ሊያስገድዳት እንደሞከረ ነገረችው። ሆኖም ይህ ውሸት ነበር። ጶጢፋር በጣም ተናደደ፤ ስለዚህ ዮሴፍን እስር ቤት አስገባው። ሆኖም ይሖዋ ዮሴፍን አልረሳውም።

“ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።”—1 ጴጥሮስ 5:6