በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 22

በቀይ ባሕር የተፈጸመው ተአምር

በቀይ ባሕር የተፈጸመው ተአምር

ፈርዖን፣ እስራኤላውያን ግብፅን ለቀው መውጣታቸውን ሲሰማ እነሱን መልቀቁ ቆጨው። ወታደሮቹን እንዲህ በማለት አዘዛቸው፦ ‘የጦር ሠረገሎቼን በሙሉ አዘጋጁና እስራኤላውያንን እናሳዳቸው! እነሱን መልቀቅ አልነበረብንም።’ ፈርዖንና አብረውት ያሉት ሰዎች እስራኤላውያንን ማሳደድ ጀመሩ።

ይሖዋ ሕዝቡን ቀን ቀን በደመና፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በእሳት ይመራቸው ነበር። ወደ ቀይ ባሕር እየመራ ወሰዳቸው፤ ከዚያም በባሕሩ አጠገብ ድንኳናቸውን እንዲተክሉ ነገራቸው።

እስራኤላውያን ዞር ብለው ሲመለከቱ ፈርዖንና ሠራዊቱ እያሳደዷቸው እንደሆነ አዩ። ከፊታቸው ባሕር፣ ከኋላቸው ደግሞ የግብፅ ሠራዊት ስላለ ማምለጫ አልነበራቸውም። ስለዚህ እንዲህ በማለት ወደ ሙሴ ጮኹ፦ ‘በቃ መሞታችን ነው! እዚያው ግብፅ ብትተወን ይሻለን ነበር።’ ሙሴ ግን ‘አትፍሩ። ይሖዋ እንዴት እንደሚያድነን ታያላችሁ’ አላቸው። በእርግጥም ሙሴ በይሖዋ ላይ ትልቅ እምነት ነበረው።

ይሖዋ እስራኤላውያንን ድንኳናቸውን ነቅለው እንዲጓዙ ነገራቸው። በዚያ ምሽት ይሖዋ ደመናው በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል እንዲሆን አደረገ። ግብፃውያን ባሉበት አካባቢ ጨለማ ነበር። እስራኤላውያን ባሉበት አካባቢ ግን ብርሃን ነበር።

 ይሖዋ ሙሴን እጁን በባሕሩ ላይ እንዲዘረጋ ነገረው። ከዚያም ይሖዋ ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ። ባሕሩ ለሁለት ተከፈለና መሃል ላይ ማለፊያ መንገድ ተከፈተ። በሚሊዮን የሚቆጠሩት እስራኤላውያን እንደ ግድግዳ በቆመው ውኃ መካከል በደረቅ መሬት ላይ ተሻገሩ።

የፈርዖን ወታደሮች እስራኤላውያንን ተከትለው ወደተከፈለው ባሕር ገቡ። ከዚያም ይሖዋ የግብፅ ወታደሮች ግራ እንዲጋቡ አደረገ። የሠረገሎቻቸው እግሮችም ወላለቁ። በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ‘ከዚህ እንውጣ! ይሖዋ እየተዋጋላቸው ነው’ በማለት ጮኹ።

ይሖዋ ሙሴን ‘እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ’ አለው። ወዲያውኑም እንደ ግድግዳ የቆመው ውኃ ተመልሶ የግብፅን ወታደሮች በሙሉ አለበሳቸው። ፈርዖንና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ሞቱ። አንዳቸውም አልተረፉም።

ባሕሩን ተሻግረው ያለፉት እስራኤላውያን ይሖዋን እንዲህ በማለት በመዝሙር አወደሱት፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ እዘምራለሁ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።” ሕዝቡ ሲዘምር ሴቶቹ ይጨፍሩና ከበሮ ይመቱ ነበር። እስራኤላውያን ከግብፃውያን ባርነት ነፃ በመውጣታቸው በጣም ተደሰቱ።

“ስለዚህ በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።”—ዕብራውያን 13:6