በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 18

በእሳት የተያያዘው ቁጥቋጦ

በእሳት የተያያዘው ቁጥቋጦ

ሙሴ በምድያም ምድር 40 ዓመት ኖረ። በዚያም ሚስት አግብቶ ልጆች ወለደ። አንድ ቀን በሲና ተራራ አጠገብ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ የሚገርም ነገር አየ። አንድ ቁጥቋጦ በእሳት ተያይዞ የነበረ ቢሆንም ቁጥቋጦው አልተቃጠለም! ሙሴ ቁጥቋጦው ለምን እንዳልተቃጠለ ለማየት ሲጠጋ ከቁጥቋጦው ውስጥ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማ፦ ‘ሙሴ! ወደዚህ አትጠጋ። የቆምክበት መሬት ቅዱስ ስለሆነ ጫማህን አውልቅ።’ ሙሴን በአንድ መልአክ አማካኝነት ያነጋገረው ይሖዋ ነበር።

በዚህ ጊዜ ሙሴ ስለፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከቁጥቋጦው ውስጥ የተሰማው ድምፅ እንዲህ አለው፦ ‘እስራኤላውያን እየደረሰባቸው ያለውን ሥቃይ አይቻለሁ። ከግብፃውያን ነፃ አውጥቼ ወደ መልካም ምድር አመጣቸዋለሁ። ሕዝቤን እየመራህ ከግብፅ የምታወጣው አንተ ነህ።’ ሙሴ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ መሆን አለበት።

ሙሴ ‘ሰዎቹ ማን ነው የላከህ ብለው ሲጠይቁኝ ምን ልበላቸው?’ አለ። አምላክም ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ነው በላቸው’ ሲል መለሰለት። ከዚያም ሙሴ ‘ሕዝቡ ባይሰማኝስ?’ ብሎ ጠየቀ። ይሖዋ ሙሴን እንደሚረዳው የሚያሳይ ማረጋገጫ ሰጠው። ሙሴን ዱላውን ወደ መሬት እንዲጥል ነገረው። በዚህ ጊዜ ዱላው እባብ ሆነ! ሙሴ የእባቡን ጅራት ሲይዘው እባቡ ተመልሶ ዱላ ሆነ። ይሖዋም ‘ይህን ተአምር ስታሳይ እኔ እንደላኩህ ያምናሉ’ አለው።

ሙሴም ‘እኔ በደንብ መናገር አልችልም’ አለ። ይሖዋም ‘ምን ማለት እንዳለብህ እነግርሃለሁ፤ እንዲሁም ወንድምህ አሮን እንዲረዳህ እልከዋለሁ’ በማለት ቃል ገባለት። ሙሴ፣ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሚሆን በመተማመን ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ወደ ግብፅ ተመለሰ።

“እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና።”—ማቴዎስ 10:19