በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 10

የሎጥን ሚስት አስታውሱ

የሎጥን ሚስት አስታውሱ

ሎጥ፣ ከአጎቱ ከአብርሃም ጋር በከነአን ምድር ይኖር ነበር። አብርሃምና ሎጥ የነበሯቸው እንስሳት በጣም እየበዙ ስለሄዱ መሬቱ ለእነዚያ ሁሉ እንስሳት ሊበቃቸው አልቻለም። ስለዚህ አብርሃም ሎጥን እንዲህ አለው፦ ‘ከዚህ በኋላ አንድ ቦታ ላይ አብረን መኖር አንችልም። እባክህ አንተ መሄድ የምትፈልግበትን ቦታ ምረጥ፤ ከዚያም እኔ ወደ ሌላ ቦታ እሄዳለሁ።’ አብርሃም እንዲህ ብሎ መናገሩ ራስ ወዳድ ሰው እንዳልነበረ ያሳያል።

ሎጥ ሰዶም በምትባል ከተማ አቅራቢያ የሚያምር አካባቢ አየ። በአካባቢው ብዙ ውኃ እንዲሁም የለመለመ ሣር ነበር። ስለዚህ ሎጥ ያንን ቦታ መርጦ ከቤተሰቡ ጋር በዚያ መኖር ጀመረ።

በሰዶምና በአቅራቢያዋ በምትገኘው በገሞራ ከተማ የሚኖሩት ሰዎች በጣም መጥፎ ነበሩ። እንዲያውም ሰዎቹ በጣም መጥፎ ከመሆናቸው የተነሳ ይሖዋ እነዚያን ከተሞች ለማጥፋት ወስኖ ነበር። ነገር ግን ይሖዋ ሎጥንና ቤተሰቡን ሊያድናቸው ስለፈለገ እንዲያስጠነቅቋቸው ሁለት መላእክት ላከ። መላእክቱም ‘ቶሎ በሉ! ከዚህች ከተማ ውጡ። ይሖዋ ከተማዋን ሊያጠፋት ነው’ አሏቸው።

ሎጥ ግን ወዲያውኑ ከከተማዋ ከመውጣት ይልቅ እዚያው ቆየ። ስለዚህ መላእክቱ ሎጥን፣ ሚስቱንና ሁለቱን ልጆቹን እጃቸውን ይዘው በፍጥነት ከከተማዋ አስወጧቸው። እንዲህም አሏቸው፦ ‘ሩጡ! ሕይወታችሁን ለማትረፍ አምልጡ፤ ወደ ኋላ አትመልከቱ። ወደ ኋላ ከተመለከታችሁ ትሞታላችሁ!’

ሎጥና ቤተሰቡ ዞአር ወደተባለች ከተማ ሲደርሱ ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ አዘነበባቸው። ሁለቱም ከተሞች ሙሉ በሙሉ ጠፉ። የሎጥ  ሚስት ይሖዋን ሳትታዘዝ ወደ ኋላ በመመልከቷ የጨው ዓምድ ሆነች! ሎጥና ሴቶች ልጆቹ ግን ይሖዋን በመታዘዛቸው በሕይወት ተረፉ። የሎጥ ሚስት ይሖዋን ባለመታዘዟ ሎጥና ልጆቹ በጣም አዝነው መሆን አለበት። ይህ ታሪክ የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምረናል።

“የሎጥን ሚስት አስታውሱ።”—ሉቃስ 17:32