በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ትምህርት 4

ቃየን ተናዶ ወንድሙን ገደለው

ቃየን ተናዶ ወንድሙን ገደለው

አዳምና ሔዋን ከኤደን የአትክልት ስፍራ ከወጡ በኋላ ብዙ ልጆችን ወለዱ። የመጀመሪያ ልጃቸው ቃየን ገበሬ ሆነ፤ ሁለተኛ ልጃቸው አቤል ደግሞ እረኛ ሆነ።

አንድ ቀን፣ ቃየንና አቤል ለይሖዋ መባ አቀረቡ። መባ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? መባ ለአምላክ የሚሰጥ ስጦታ ነው። ይሖዋ አቤል ባቀረበው መባ የተደሰተ ቢሆንም ቃየን ባቀረበው መባ ግን አልተደሰተም። ይህም ቃየንን በጣም አናደደው። ይሖዋ ቃየንን ንዴቱ መጥፎ ነገር እንዲፈጽም ሊያደርገው እንደሚችል አስጠነቀቀው። ቃየን ግን ይሖዋ ያለውን አልሰማም።

ቃየን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። ሜዳ ላይ ብቻቸውን ሳሉ ቃየን ወንድሙን መታውና ገደለው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ? ይሖዋ ቃየንን  ከቤተሰቡ ተለይቶ ወደ ሩቅ ቦታ እንዲሄድ በማድረግ ቀጣው። ቃየን ተመልሶ እንዳይመጣ ተከልክሎ ነበር።

ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ነገሮች እኛ እንደፈለግነው ሳይሆኑ ሲቀሩ ልንናደድ እንችላለን። ሰዎች መናደዳችንን ተመልክተው ምክር ሊሰጡን ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ እንደተናደድን እኛ ራሳችን ሊታወቀን ይችላል። በዚህ ጊዜ መጥፎ ነገር ከማድረጋችን በፊት ቶሎ ንዴታችንን ለማብረድ ጥረት ማድረግ አለብን።

አቤል ይሖዋን ይወድና ትክክል የሆነውን ነገር ያደርግ ስለነበር ይሖዋ ሁልጊዜም ያስታውሰዋል። አምላክ ምድርን ገነት ሲያደርግ አቤልን ከሞት ያስነሳዋል።

“በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።”—ማቴዎስ 5:24