መራመድ የማይችል አንድ ሰው በየቀኑ በቤተ መቅደሱ በር አጠገብ ተቀምጦ ይለምን ነበር። አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲገቡ አያቸው። እሱም ‘እባካችሁ ገንዘብ ስጡኝ’ ብሎ ለመናቸው። ጴጥሮስም ‘ከገንዘብ የበለጠ ነገር እሰጥሃለሁ። በኢየሱስ ስም ተነሳና ተራመድ!’ አለው። ከዚያም ጴጥሮስ እጁን ይዞ አስነሳው፤ ሰውየውም መራመድ ጀመረ! ሕዝቡ ይህን ተአምር ሲያዩ በጣም ተደሰቱ፤ ብዙ ሰዎችም በኢየሱስ አመኑ።

ካህናትና ሰዱቃውያን ግን በጣም ተናደዱ። ሐዋርያቱንም ይዘው ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ ወሰዷቸው፤ ከዚያም ‘ይህን ሰው እንድትፈውሱ ሥልጣን የሰጣችሁ ማን ነው?’ ብለው ጠየቋቸው። ጴጥሮስም ‘ይህን ሥልጣን የሰጠን እናንተ የገደላችሁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው’ በማለት መለሰላቸው። የሃይማኖት መሪዎቹ በቁጣ ‘ስለ ኢየሱስ መናገራችሁን አቁሙ!’ አሏቸው። ሐዋርያቱ ግን እንዲህ አሉ፦ ‘ስለ እሱ መናገር አለብን። ስለ ኢየሱስ መናገራችንን ልናቆም አንችልም።’

ጴጥሮስና ዮሐንስ እንደተለቀቁ ወደ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሄደው የተፈጠረውን ነገር ነገሯቸው። ከዚያም እንዲህ በማለት አብረው ወደ ይሖዋ ጸለዩ፦ ‘የሰጠኸንን ሥራ ማከናወናችንን መቀጠል እንድንችል እባክህ ድፍረት ስጠን።’ ይሖዋም መንፈስ ቅዱስን ሰጣቸው፤ እነሱም መስበካቸውንና የታመሙትን መፈወሳቸውን ቀጠሉ። ሌሎች ብዙ ሰዎችም በኢየሱስ አመኑ። ሰዱቃውያን በጣም ስለቀኑ ሐዋርያቱን ይዘው እስር ቤት አስገቧቸው። ሆኖም ሌሊት ላይ ይሖዋ አንድ መልአክ ላከ፤ መልአኩም የእስር ቤቱን በሮች ከፍቶ አስወጣቸውና ሐዋርያቱን ‘ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳችሁ በዚያ ማስተማራችሁን ቀጥሉ’ አላቸው።

በቀጣዩ ቀን ጠዋት ሰዎች የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት የሆኑትን የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ አሏቸው፦ ‘የእስር ቤቱ በሮች እንደተቆለፉ ናቸው፤ ያሰራችኋቸው ሰዎች ግን እስር ቤቱ ውስጥ የሉም! ቤተ መቅደሱ ውስጥ ቆመው ሕዝቡን እያስተማሩ ነው!’ ከዚያም ሐዋርያቱ በድጋሚ ተይዘው በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ቀረቡ። ሊቀ ካህናቱም  ‘ስለ ኢየሱስ እንዳትናገሩ አዘናችሁ አልነበረም?’ አላቸው። ጴጥሮስ ግን “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት መለሰ።

የሃይማኖት መሪዎቹ በጣም ስለተናደዱ ሐዋርያቱን መግደል ፈለጉ። ሆኖም ገማልያል የተባለ አንድ ፈሪሳዊ ተነስቶ እንዲህ አላቸው፦ ‘ተጠንቀቁ! አምላክ እነዚህን ሰዎች እየረዳቸው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ከአምላክ ጋር መጣላት ትፈልጋላችሁ?’ የሃይማኖት መሪዎቹም የገማልያልን ምክር ሰሙ። ሐዋርያቱን ከገረፏቸው በኋላ መስበካቸውን እንዲያቆሙ በድጋሚ አዘዟቸው፤ ከዚያም ለቀቋቸው። ይህም ቢሆን ሐዋርያቱን ሊያስቆማቸው አልቻለም። በቤተ መቅደስም ሆነ ከቤት ወደ ቤት ምሥራቹን በድፍረት መስበካቸውን ቀጠሉ።

“ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።”—የሐዋርያት ሥራ 5:29