ሐዋርያው ዮሐንስ ጳጥሞስ በምትባል ደሴት ታስሮ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚገልጹ 16 ራእዮችን አሳየው። እነዚህ ራእዮች የይሖዋ ስም የሚቀደሰው፣ መንግሥቱ የሚመጣውና ፈቃዱ በሰማይም ሆነ በምድር የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ ይገልጻሉ።

ዮሐንስ በአንዱ ራእዩ ላይ ይሖዋ በሰማይ ባለው ክብራማ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ተመልክቷል፤ በዙፋኑ ዙሪያ ነጭ ልብስ የለበሱና የወርቅ ዘውድ ያደረጉ 24 ሽማግሌዎች ነበሩ። የመብረቅ ብልጭታና የነጎድጓድ ድምፅ ከዙፋኑ ይወጣል። በዙፋኑ ዙሪያ ያሉት 24 ሽማግሌዎች በይሖዋ ፊት ተደፍተው ያመልኩታል። በሌላ ራእይ ላይ ደግሞ ዮሐንስ ከሁሉም ብሔራት፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ ይሖዋን የሚያመልኩ እጅግ ብዙ ሰዎች ተመልክቷል። ‘በጉ’ ተብሎ የተገለጸው ኢየሱስም እነዚህን ሰዎች ይንከባከባቸዋል፤ እንዲሁም ወደ ሕይወት ውኃ ይወስዳቸዋል። ዮሐንስ በኋላ ባየው ሌላ ራእይ ላይ ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ከ24ቱ ሽማግሌዎች ጋር ሲገዛ ተመልክቷል። በቀጣዩ ራእይ ላይ ደግሞ ኢየሱስ በዘንዶ ከተመሰለው ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ሲዋጋ አይቷል። ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ወደ ምድር ወርውሯቸዋል።

 ቀጥሎም ዮሐንስ፣ በጉ ከ144,000ዎቹ ጋር በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ተመልክቷል። እንዲሁም አንድ መልአክ ሰዎች አምላክን እንዲፈሩና ክብር እንዲሰጡት እየተናገረ በምድር ዙሪያ ሲበር አይቷል።

በቀጣዩ ራእይ ላይ ደግሞ የአርማጌዶን ጦርነት ሲካሄድ ተመለከተ። በዚህ ጦርነት ኢየሱስና ሠራዊቱ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ያጠፋሉ። በመጨረሻው ራእይ ላይ ዮሐንስ በሰማይና በምድር ፍጹም ሰላም ሰፍኖ ተመለከተ። ሰይጣንም ሆነ ተከታዮቹ ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ሁሉ ቅዱስ የሆነውን የይሖዋን ስም ከፍ አድርገው ይመለከታሉ፤ እንዲሁም እሱን ብቻ ያመልካሉ።

“በአንተና በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።”—ዘፍጥረት 3:15