በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 98

ክርስትና ወደ ብዙ አገሮች ተስፋፋ

ክርስትና ወደ ብዙ አገሮች ተስፋፋ

የኢየሱስ ሐዋርያት ምሥራቹን በመላው ምድር እንዲያስፋፉ ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል። በ47 ዓ.ም. በአንጾኪያ የሚኖሩ ወንድሞች ጳውሎስንና በርናባስን ወደተለያዩ ቦታዎች ሄደው እንዲሰብኩ ላኳቸው። እነዚህ ሁለት ቀናተኛ ሰባኪዎች ደርቤን፣ ልስጥራንና ኢቆንዮንን ጨምሮ በትንሿ እስያ ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ሄዱ።

ጳውሎስና በርናባስ ሀብታም፣ ድሃ፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳይሉ ለሁሉም ሰው ይሰብኩ ነበር። ብዙ ሰዎች ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውነት ተቀበሉ። ጳውሎስና በርናባስ የቆጵሮስ አገረ ገዢ ለሆነው ለሰርግዮስ ጳውሎስ በሰበኩበት ወቅት አንድ ጠንቋይ ሊያስቆማቸው ሞከረ። ጳውሎስ ግን ጠንቋዩን ‘ይሖዋ ይቀጣሃል’ አለው። ወዲያውኑም ጠንቋዩ ዓይኑ ታወረ። አገረ ገዢው ሰርግዮስ ጳውሎስም ይህን ሲያይ አማኝ ሆነ።

ጳውሎስና በርናባስ በሁሉም ቦታ ማለትም ከቤት ወደ ቤት፣ በገበያ ቦታዎች፣ በመንገድ ላይና በምኩራቦች ውስጥ ይሰብኩ ነበር። ልስጥራ ውስጥ አንድን ሽባ ሰው በፈወሱ ጊዜ ይህን ተአምር ሲፈጽሙ ያዩ ሰዎች ጳውሎስና በርናባስ አማልክት ስለመሰሏቸው እነሱን ለማምለክ ተነሳሱ። ጳውሎስና በርናባስ ግን ‘አምላክን ብቻ አምልኩ! እኛ እንደ እናንተው ሰዎች ነን’ በማለት ከለከሏቸው። ከዚያም አንዳንድ አይሁዳውያን መጥተው ሕዝቡ በጳውሎስ ላይ እንዲያምፅ አደረጉ። ሰዎቹም ጳውሎስን በድንጋይ ወገሩት። ከዚያም ከከተማዋ ጎትተው አወጡት፤ የሞተ ስለመሰላቸውም ጥለውት ሄዱ። ጳውሎስ ግን አልሞተም ነበር! ወዲያውኑ ወንድሞች መጥተው ጳውሎስን ይዘውት ወደ ከተማዋ ገቡ። በኋላም ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ።

በ49 ዓ.ም. ጳውሎስ በተለያዩ ቦታዎች ለመስበክ እንደገና ተጓዘ። በትንሿ እስያ ወደሚገኙት ወንድሞች በድጋሚ ከሄደ በኋላ ምሥራቹን ርቀው በሚገኙት  የአውሮፓ ከተሞች ሰበከ። ወደ አቴንስ፣ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ ተሰሎንቄና ሌሎች ቦታዎች ሄዷል። ሲላስ፣ ሉቃስ እንዲሁም ጢሞቴዎስ የተባለ አንድ ወጣት ከጳውሎስ ጋር አብረው ተጉዘዋል። ጉባኤዎችን በማቋቋምና በማጠናከር አብረው ሠርተዋል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያሉትን ወንድሞች በማበረታታት ለአንድ ዓመት ከግማሽ ያህል በዚያ ቆየ። በዚህ ወቅት ምሥራቹን ይሰብክና ሰዎችን ያስተምር ነበር፤ እንዲሁም ለተለያዩ ጉባኤዎች ደብዳቤ ጽፏል። በተጨማሪም ድንኳን ይሠራ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ።

በ52 ዓ.ም. ጳውሎስ በተለያዩ ቦታዎች ለመስበክ ለሦስተኛ ጊዜ ተጓዘ፤ መጀመሪያ የተጓዘው ወደ ትንሿ እስያ ነበር። በስተ ሰሜን እስከ ፊልጵስዩስ ድረስ የሄደ ሲሆን ከዚያም ወደ ቆሮንቶስ ተጓዘ። ጳውሎስ እያስተማረ፣ የታመሙትን እየፈወሰና ጉባኤውን እየረዳ ለተወሰኑ ዓመታት በኤፌሶን ቆየ። በተጨማሪም በየቀኑ በአንድ ትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ ንግግር ይሰጥ ነበር። ብዙ ሰዎች የሚያስተምረውን ትምህርት በመስማት ሕይወታቸውን መለወጥ ችለዋል። ጳውሎስ በብዙ አገሮች ምሥራቹን ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ።

“ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።”—ማቴዎስ 28:19