ሳኦል ጠርሴስ ውስጥ የተወለደ የሮም ዜጋ ነው። የአይሁዳውያንን ሕግ ጠንቅቆ የሚያውቅ ፈሪሳዊ ሲሆን ክርስቲያኖችን በጣም ይጠላል። ክርስቲያን የሆኑ ወንዶችንና ሴቶችን ከቤታቸው እየወሰደ እስር ቤት ያስገባቸው ነበር። በቁጣ የተሞሉ ሰዎች እስጢፋኖስ የተባለውን ደቀ መዝሙር በድንጋይ ወግረው በገደሉት ወቅትም ሳኦል ቆሞ ይመለከት ነበር።

ሆኖም ሳኦል በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖችን በማሰር ብቻ አላበቃም። በደማስቆ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ለመያዝ ስለፈለገ ወደዚያ እንዲልከው ሊቀ ካህናቱን ጠየቀ። ሳኦል ወደ ደማስቆ ሲቃረብ በድንገት ደማቅ ብርሃን በዙሪያው አንጸባረቀ፤ እሱም መሬት ላይ ወደቀ። ከዚያም ‘ሳኦል፣ ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማ። ሳኦልም ‘አንተ ማን ነህ?’ በማለት ጠየቀ። የተሰማውም ድምፅ ‘እኔ ኢየሱስ ነኝ። አሁን ወደ ከተማዋ ግባ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ይነገርሃል’ አለው። ወዲያውኑ የሳኦል ዓይን ታወረ፤ ሰዎችም እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ከተማዋ ወሰዱት።

ደማስቆ ውስጥ ሐናንያ የሚባል አንድ ታማኝ ክርስቲያን ነበር። ኢየሱስ ሐናንያን በራእይ እንዲህ አለው፦ ‘ቀጥተኛ በተባለው መንገድ ላይ ወደሚገኘው ወደ ይሁዳ ቤት ሂድ፤ በዚያም ሳኦል የሚባለውን ሰው ፈልግ።’ ሐናንያም ‘ጌታ ሆይ፣ ስለዚህ ሰው በደንብ አውቃለሁ! ደቀ መዛሙርትህን ወደ እስር ቤት እያስገባ ያለ ሰው ነው!’ አለው። ኢየሱስ ግን መልሶ ‘ወደ እሱ ሂድ። ሳኦልን ለብዙ አገር ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰብክ መርጬዋለሁ’ አለው።

ስለዚህ ሐናንያ ወደ ሳኦል ሄዶ ‘ወንድሜ ሳኦል፣ ኢየሱስ ዓይንህን እንድከፍትልህ ልኮኛል’ አለው። ወዲያውኑ ሳኦል ማየት ቻለ። ከዚያም ስለ ኢየሱስ ተማረና የእሱ ተከታይ ሆነ። ሳኦል ክርስቲያን ሆኖ ከተጠመቀ በኋላ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ሆኖ በምኩራቦች ውስጥ መስበክ ጀመረ። አይሁዳውያን ሳኦል ሰዎችን ስለ ኢየሱስ ሲያስተምር ሲያዩ ምን ያህል ደንግጠው ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ!  ‘የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት እየፈለገ ሲያስር የነበረው ሰው ይህ አይደለም እንዴ?’ ይሉ ነበር።

ሳኦል ለሦስት ዓመት ያህል በደማስቆ ለሚኖሩ ሰዎች ሰበከ። አይሁዳውያን ሳኦልን በጣም ስለጠሉት ሊገድሉት አሰቡ። ወንድሞች ግን ይህን ስላወቁ ሳኦልን እንዲያመልጥ ረዱት። ሳኦልን ቅርጫት ውስጥ ከተቱትና በከተማዋ አጥር ላይ ባለ ክፍተት በኩል አሾልከው አወረዱት።

ሳኦል ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ እዚያ ካሉት ወንድሞች ጋር ለመቀላቀል ሞከረ። ሆኖም ወንድሞች ሳኦልን ፈሩት። ከዚያም በርናባስ የተባለ አንድ ደግ ደቀ መዝሙር ሳኦልን ወደ ሐዋርያት ወስዶ ምን ያህል እንደተለወጠ ገለጸላቸው። ሳኦልም በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ጉባኤ ጋር አብሮ ምሥራቹን በቅንዓት መስበክ ጀመረ። በኋላም ጳውሎስ የሚል ስም ተሰጠው።

“‘ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ’ . . . ከኃጢአተኞች ደግሞ እኔ ዋነኛ ነኝ።”—1 ጢሞቴዎስ 1:15