በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ትምህርት 97

ቆርኔሌዎስ መንፈስ ቅዱስ ተቀበለ

ቆርኔሌዎስ መንፈስ ቅዱስ ተቀበለ

ቂሳርያ ውስጥ የሚኖር ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ የሮም የጦር መኮንን ነበር። ቆርኔሌዎስ አይሁዳዊ ባይሆንም እንኳ አይሁዳውያን ያከብሩት ነበር። ድሆችንና የተቸገሩ ሰዎችን በልግስና የሚረዳ ሰው ነበር። በይሖዋ ያምን የነበረ ሲሆን አዘውትሮ ወደ ይሖዋ ይጸልያል። አንድ ቀን አንድ መልአክ ለቆርኔሌዎስ ተገልጦ እንዲህ አለው፦ ‘አምላክ ጸሎትህን ሰምቷል። አሁን ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስን አስጠራው።’ ቆርኔሌዎስም ወዲያውኑ በስተ ደቡብ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኢዮጴ ሦስት ሰዎችን ላከ።

በዚህ መሃል ጴጥሮስም አንድ ራእይ ተመለከተ። ጴጥሮስ በራእዩ ላይ እንስሳትን የተመለከተ ሲሆን እነዚህን እንስሳት አይሁዳውያን እንዳይበሉ ተከልክለው ነበር፤ ሆኖም አንድ ድምፅ እንስሳቱን እንዲበላ ነገረው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ‘እኔ የረከሰ ነገር በልቼ አላውቅም’ በማለት ለመብላት ፈቃደኛ አለመሆኑን ገለጸ። ድምፁም ‘እነዚህን እንስሳት የረከሱ ብለህ አትጥራ። አምላክ ንጹሕ አድርጓቸዋል’ አለው። ከዚያም ጴጥሮስን ‘አሁን በርህ ላይ ሦስት ሰዎች ቆመዋል። ከእነሱ ጋር አብረህ ሂድ’ አለው። ጴጥሮስ ወደ በሩ በመሄድ በዚያ የቆሙትን ሰዎች ለምን እንደመጡ ጠየቃቸው። ሰዎቹም ‘የሮም የጦር መኮንን የሆነው ቆርኔሌዎስ ልኮን ነው። በቂሳርያ ወደሚገኘው ቤቱ እንድትመጣ  ይፈልጋል’ አሉት። ጴጥሮስም ሰዎቹን እዚያው እንዲያድሩ ጋበዛቸው። ከዚያም በቀጣዩ ቀን ከእነሱ ጋር ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ በኢዮጴ የሚኖሩ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ።

ቆርኔሌዎስ ጴጥሮስን ሲያየው ፊቱ ተንበረከከ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ተነስ! እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ። አይሁዳውያን ሌላ ዘር ያላቸው ሰዎች ቤት ባይገቡም እንኳ አምላክ ወደ ቤትህ እንድመጣ ነገረኝ። እባክህ ለምን እንዳስጠራኸኝ ንገረኝ።’

ቆርኔሌዎስም ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ ‘ከአራት ቀን በፊት ወደ አምላክ እየጸለይኩ ሳለ አንድ መልአክ ተገልጦልኝ አንተን እንዳስጠራህ ነገረኝ። እባክህ የይሖዋን ቃል አስተምረን።’ ጴጥሮስም እንዲህ አለ፦ ‘አምላክ እንደማያዳላ ተገንዝቤያለሁ። እሱን ማምለክ የሚፈልግን ሰው ሁሉ ይቀበላል።’ ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ብዙ ነገር አስተማራቸው። ከዚያም በቆርኔሌዎስና አብረውት በነበሩት ሰዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በኋላም ሁሉም ተጠመቁ።

“ከየትኛውም ብሔር ቢሆን [አምላክን] የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—የሐዋርያት ሥራ 10:35