በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 89

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ራት በበላበት ወቅት ‘ዛሬ ሌሊት ሁላችሁም ትታችሁኝ ትሄዳላችሁ’ ብሏቸው ነበር። ከዚያም ጴጥሮስ ‘እኔ አልተውህም! ሌሎቹ ሁሉ ቢተዉህ እንኳ እኔ ግን መቼም ትቼህ አልሄድም’ አለው። ኢየሱስ ግን ‘ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ “አላውቀውም” ብለህ ትክደኛለህ’ አለው።

ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ ቀያፋ ቤት ሲወስዱት አብዛኞቹ ሐዋርያት ሸሽተው ነበር። ከሐዋርያቱ መካከል ሁለቱ ግን ተከትለውት ሄዱ። ከእነሱ አንዱ ጴጥሮስ ነበር። ጴጥሮስ ወደ ቀያፋ ግቢ ገባና እሳት የተቀጣጠለበት ቦታ ጋ ሄዶ መሞቅ ጀመረ። አንዲት አገልጋይ ጴጥሮስን አየችውና ‘አንተን አውቅሃለሁ! ከኢየሱስ ጋር ነበርክ!’ አለችው።

ጴጥሮስ ግን ‘አልነበርኩም! ስለ ምን እንደምታወሪ አላውቅም!’ አላት። ከዚያም ወደ ግቢው መግቢያ ሄደ። በዚያም አንዲት ሌላ አገልጋይ አየችውና ‘ይህ ሰው ከኢየሱስ ጋር ነበር!’ አለች። ጴጥሮስ ግን ‘ኢየሱስን ፈጽሞ አላውቀውም!’ አለ። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ‘አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ! ልክ እንደ ኢየሱስ የገሊላ ሰው እንደሆንክ አነጋገርህ ያስታውቃል’ አለው። ጴጥሮስ ግን ‘ኢየሱስን አላውቀውም!’ ብሎ ማለ።

ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። ከዚያም ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ዞር ብሎ ሲመለከተው አየ። በዚህ ጊዜ፣ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ትዝ አለው፤ ስለዚህ ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

በዚህ ወቅት የሳንሄድሪን ሸንጎ የተባለው የአይሁዳውያን ፍርድ ቤት አባላት በኢየሱስ ላይ ለመፍረድ በቀያፋ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመግደል አስቀድመው ወስነው ስለነበር ለመግደል የሚያስችላቸውን ሰበብ መፈለግ ጀመሩ። ሆኖም እሱን መክሰስ የሚችሉበት ነገር አላገኙም። በመጨረሻም ቀያፋ በቀጥታ ኢየሱስን ‘የአምላክ ልጅ ነህ?’ ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም ‘አዎ፣ ነኝ’ ብሎ መለሰ። ከዚያም ቀያፋ ‘ከዚህ ሌላ ምን ማስረጃ ያስፈልጋል? ይህ ሰው አምላክን እየተሳደበ ነው!’ አለ። የፍርድ ቤቱ አባላትም ‘ይህ ሰው መሞት ይገባዋል’ አሉ። ከዚያም ኢየሱስን በጥፊ መቱት፤ ተፉበት፤  እንዲሁም ዓይኑን ሸፍነው እየመቱት ‘እስቲ ነቢይ ከሆንክ የመታህ ማን እንደሆነ ተናገር!’ ይሉት ነበር።

ሲነጋም ኢየሱስን ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ አዳራሽ ወስደው በድጋሚ ‘አንተ የአምላክ ልጅ ነህ?’ ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም ‘የአምላክ ልጅ መሆኔን እናንተው ራሳችሁ እየተናገራችሁ ነው’ አላቸው። ከዚያም ‘አምላክን ተሳድቧል’ በማለት ወደ ሮማዊው አገረ ገዢ ወደ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ቤተ መንግሥት ወሰዱት። ከዚያ በኋላ ምን ሆነ? እስቲ እንመልከት።

“ሁላችሁም ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን ትታችሁ የምትሄዱበት ሰዓት . . . ደርሷል። ይሁንና አብ ከእኔ ጋር ስላለ ብቻዬን አይደለሁም።”—ዮሐንስ 16:32