በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 78

ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሰበከ

ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሰበከ

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‘የአምላክ መንግሥት ቀርቧል’ በማለት መስበክ ጀመረ። በገሊላና በይሁዳ ውስጥ ሲዘዋወር ደቀ መዛሙርቱ ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ፣ ወዳደገባት ከተማ ወደ ናዝሬት ሲመለስ ወደ ምኩራብ ሄደ፤ በዚያም የኢሳይያስን መጽሐፍ ጥቅልል ዘርግቶ ‘ይሖዋ ምሥራች እንድሰብክ መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶኛል’ በማለት ጮክ ብሎ አነበበ። ኢየሱስ ይህን የጠቀሰው ለምንድን ነው? ሕዝቡ ኢየሱስ ተአምራት ሲፈጽም ማየት ፈልገው የነበረ ቢሆንም እሱ መንፈስ ቅዱስን የተቀበለበት ዋነኛ ዓላማ ምሥራቹን ለመስበክ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ስለፈለገ ነው። ከዚያም የሚሰሙትን ሰዎች ‘ይህ ትንቢት ዛሬ ተፈጸመ’ አላቸው።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ፤ በዚያም አራት ዓሣ አጥማጆችን አገኘ። እነሱም ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ሲሆኑ ከጊዜ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሆነዋል። ኢየሱስም “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያውኑ ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ትተው ኢየሱስን ተከተሉት። በመላው ገሊላ እየተዘዋወሩ ስለ ይሖዋ መንግሥት ሰበኩ። በምኩራቦች፣ በገበያ ቦታዎችና በየመንገዱ ይሰብኩ ነበር። በሄዱበት ቦታ ሁሉ ብዙ ሕዝብ ይከተላቸው ነበር። ስለ ኢየሱስ የሚወራው ወሬ እስከ ሶርያ ድረስ ተሰማ።

ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ለአንዳንድ ተከታዮቹ የታመሙ ሰዎችን የማዳንና አጋንንትን የማስወጣት ኃይል ሰጣቸው። ሌሎች ደግሞ ምሥራቹን እየሰበከ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ሲሄድ አብረውት ይጓዙ ነበር። መግደላዊት ማርያምን፣ ዮሐናንና ሶስናን ጨምሮ ብዙ ታማኝ ሴቶች ኢየሱስንና ተከታዮቹን ይንከባከቧቸው ነበር።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ካሠለጠናቸው በኋላ እንዲሰብኩ ላካቸው። በገሊላ ውስጥ እየተዘዋወሩ ሲሰብኩ ሌሎች ብዙ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ተጠመቁ። የኢየሱስ ተከታዮች መሆን የሚፈልጉት ሰዎች ቁጥር በጣም ብዙ ስለነበር ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ለአጨዳ ከደረሰ እርሻ ጋር አመሳስሏቸዋል። ‘እህሉን የሚሰበስቡ ተጨማሪ ሰዎችን እንዲልክ ወደ ይሖዋ ጸልዩ’ ሲል ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ 70 ደቀ መዛሙርት መረጠና በመላው ይሁዳ እንዲሰብኩ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። እነሱም ስለ አምላክ መንግሥት  የሚገልጸውን ምሥራች ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ተናገሩ። ደቀ መዛሙርቱ ሲሰብኩ ያጋጠሟቸውን ነገሮች ለኢየሱስ ለመናገር በጣም ጓጉተው ነበር። ዲያብሎስ የስብከቱን ሥራ ማስቆም አልቻለም።

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን አስፈላጊ ሥራ መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ አድርጓል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ ‘በመላው ምድር ምሥራቹን ስበኩ። ሰዎችን ስለ አምላክ ቃል አስተምሯቸው እንዲሁም አጥምቋቸው።’

“ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው።”—ሉቃስ 4:43