በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 83

ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን መገበ

ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን መገበ

ጊዜው 32 ዓ.ም. ሲሆን የፋሲካ በዓል የሚከበርበት ወቅት ተቃርቧል፤ ሐዋርያቱ በተለያዩ ቦታዎች ሲሰብኩ ቆይተው ወደ ኢየሱስ ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱ በጣም ደክሟቸው ስለነበር እረፍት እንዲያደርጉ ኢየሱስ በጀልባ ወደ ቤተሳይዳ ይዟቸው ሄደ። ሆኖም ጀልባው ባሕሩ ዳር ሲደርስ ኢየሱስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተከትለዋቸው እንደመጡ አየ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ መሆን ፈልጎ የነበረ ቢሆንም ሰዎቹን ሲመለከት አዘነላቸው። በመሆኑም የታመሙትን ሰዎች ፈወሰ፤ ከዚያም ያስተምራቸው ጀመር። ኢየሱስ ቀኑን ሙሉ ስለ አምላክ መንግሥት ሲያስተምራቸው ቆየ። ቀኑ እየመሸ ሲሄድ ሐዋርያቱ ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ አሉት፦ ‘ሰዎቹ ርቧቸዋል። ሄደው የሚበሉት ምግብ ቢገዙ አይሻልም?’

ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ ‘መሄድ አያስፈልጋቸውም። የሚበሉት ነገር ስጧቸው።’ ሐዋርያቱም ‘ሄደን ለእነሱ የሚሆን ዳቦ እንድንገዛ ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት። ከሐዋርያቱ አንዱ የሆነው ፊልጶስም ‘የ200 ዲናር ዳቦ ብንገዛ እንኳ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ አይበቃም’ አለ።

ኢየሱስ ‘እናንተ ምን የሚበላ ነገር ይዛችኋል?’ ብሎ ጠየቃቸው። እንድርያስም ‘አምስት ዳቦና ሁለት ትናንሽ ዓሣ አለን። ይህ ግን በምንም ዓይነት ለሕዝቡ ሊበቃ አይችልም’ አለ። ኢየሱስም ‘ዳቦውንና ዓሣውን አምጡልኝ’ አላቸው። ከዚያም ሰዎቹ ሣሩ ላይ ሃምሳ ሃምሳና መቶ መቶ እየሆኑ በቡድን እንዲቀመጡ ነገራቸው። ኢየሱስ ዳቦውንና ዓሣውን ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ጸለየ። ከዚያም ምግቡን ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፤ እነሱም ለሕዝቡ አከፋፈሉ። በቦታው የነበሩት 5,000 ወንዶች እንዲሁም ብዙ ሴቶችና ልጆች እስኪጠግቡ  ድረስ በሉ። በኋላም ሐዋርያቱ የተረፈው ምግብ እንዳይባክን ሰበሰቡት። የተረፈው ምግብ 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ! ይህ በጣም አስገራሚ የሆነ ተአምር ነው!

ሕዝቡ በጣም ስለተደነቁ ኢየሱስን ንጉሣቸው ሊያደርጉት ፈለጉ። ሆኖም ኢየሱስ፣ ይሖዋ እሱን የሚያነግሥበት ጊዜ እንዳልደረሰ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ሰዎቹ ወደየአካባቢያቸው እንዲሄዱ ካደረገ በኋላ ሐዋርያቱን የገሊላን ባሕር አቋርጠው እንዲሻገሩ ነገራቸው። ስለዚህ እነሱ በጀልባ ተጓዙ፤ ኢየሱስ ደግሞ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። ለምን? ወደ አባቱ መጸለይ ስለፈለገ ነው። ኢየሱስ ምንም ያህል ሥራ ቢበዛበት ለጸሎት ጊዜ ይመድብ ነበር።

“ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ።”—ዮሐንስ 6:27