በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 69

ገብርኤል ማርያምን አነጋገራት

ገብርኤል ማርያምን አነጋገራት

ኤልሳቤጥ ማርያም የምትባል አንዲት ወጣት ዘመድ ነበረቻት፤ ማርያም የምትኖረው በገሊላ በምትገኘው በናዝሬት ከተማ ነበር። ማርያም የአናጺነት ሙያ የነበረው ዮሴፍ የተባለ እጮኛ ነበራት። ኤልሳቤጥ የስድስት ወር እርጉዝ በነበረችበት ወቅት መልአኩ ገብርኤል ማርያምን አነጋገራት። እንዲህ አላት፦ ‘ማርያም፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን። ይሖዋ እጅግ ባርኮሻል።’ ማርያም፣ ገብርኤል ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባትም። ከዚያም እንዲህ አላት፦ ‘ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤ ስሙን ኢየሱስ ትይዋለሽ። እሱም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። መንግሥቱም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።’

ማርያምም ‘እኔ እኮ ከወንድ ጋር ተኝቼ አላውቅም። ታዲያ እንዴት ልጅ ልወልድ እችላለሁ?’ አለችው። ገብርኤልም እንዲህ አላት፦ ‘ይሖዋ የሚያቅተው ነገር የለም። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ ከዚያም ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። ዘመድሽ ኤልሳቤጥም አርግዛለች።’ ማርያምም ‘እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ። ልክ እንደተናገርከው ይሁንልኝ’ አለች።

 ማርያም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በተራራ ላይ ወደምትገኝ አንዲት ከተማ ሄደች። ኤልሳቤጥ የማርያምን ሰላምታ ስትሰማ በሆዷ ውስጥ ያለው ልጅ ዘለለ። በዚህ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እንዲህ አለች፦ ‘ማርያም፣ ይሖዋ ባርኮሻል። የመሲሑ እናት ወደ ቤቴ መምጣቷ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው።’ ማርያምም ‘በሙሉ ልቤ ይሖዋን አወድሰዋለሁ’ አለች። ማርያም ለሦስት ወር ያህል ከኤልሳቤጥ ጋር ቆየች፤ ከዚያም በናዝሬት ወደሚገኘው ቤቷ ተመለሰች።

ዮሴፍ፣ ማርያም ማርገዟን ሲያውቅ ከሌላ ወንድ ያረገዘች ስለመሰለው ሊተዋት አሰበ። ሆኖም አንድ መልአክ በሕልም ተገልጦለት ‘ማርያምን ለማግባት አትፍራ። ምንም የሠራችው ጥፋት የለም’ አለው። ስለዚህ ዮሴፍ ማርያምን አገባት፤ ወደ ቤቱም ወሰዳት።

“በሰማይና በምድር . . . ይሖዋ ደስ ያሰኘውን ነገር ሁሉ ያደርጋል።”—መዝሙር 135:6