በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 68

ኤልሳቤጥ ልጅ ወለደች

ኤልሳቤጥ ልጅ ወለደች

የኢየሩሳሌም አጥር ዳግመኛ ከተገነባ ከ400 የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል፤ በዚህ ወቅት ዘካርያስ የተባለ ካህንና ሚስቱ ኤልሳቤጥ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ይኖሩ ነበር። ከተጋቡ ረጅም ጊዜ ቢሆናቸውም እንኳ ልጅ አልነበራቸውም። አንድ ቀን ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ ዕጣን እያጠነ ሳለ መልአኩ ገብርኤል ተገለጠለት። ዘካርያስ በጣም ደነገጠ፤ ገብርኤል ግን እንዲህ አለው፦ ‘አትፍራ። ከይሖዋ የተላከ መልካም ዜና ይዤልህ መጥቻለሁ። ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙም ዮሐንስ ይባላል። ይሖዋ ዮሐንስን ልዩ ሥራ እንዲሠራ መርጦታል።’ ዘካርያስም እንዲህ በማለት ጠየቀ፦ ‘የተናገርከው ነገር እንደሚፈጸም እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ? እኔና ሚስቴ በጣም ስላረጀን ልጅ መውለድ አንችልም።’ ገብርኤልም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘ይህን መልእክት እንድነግርህ የላከኝ አምላክ ነው። ሆኖም እኔ የተናገርኩትን ስላላመንክ ልጁ እስኪወለድ ድረስ ዱዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።’

ዘካርያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ቆየ። ስለዚህ ከቤተ መቅደሱ ሲወጣ ውጭ ይጠብቁት የነበሩት ሰዎች ምን እንደገጠመው ለማወቅ ፈለጉ። ዘካርያስ ግን መናገር ስላልቻለ በእጁ ምልክት ሰጣቸው። ከዚያም ሰዎቹ ዘካርያስ ከአምላክ የመጣ መልእክት እንደተነገረው አወቁ።

ከጊዜ በኋላ ኤልሳቤጥ አረገዘችና ልክ መልአኩ እንደተናገረው ወንድ ልጅ ወለደች። ጓደኞቿና ዘመዶቿም ልጁን ለማየት መጡ። ኤልሳቤጥ ልጅ በመውለዷ በጣም ተደሰቱ። እሷም ‘የልጁ ስም ዮሐንስ ይባላል’ አለች። እነሱ ግን ‘ከዘመዶችሽ መካከል ዮሐንስ የሚባል የለም። እሱም እንደ አባቱ ዘካርያስ ይባል’ አሏት። ዘካርያስ ግን ‘ስሙ ዮሐንስ ነው’ ብሎ ጻፈ። በዚህ ጊዜ ዘካርያስ እንደገና መናገር ቻለ! ይህ ወሬ በመላዋ ይሁዳ ተዳረሰ፤ ሕዝቡም ‘ይህ ልጅ ሲያድግ ምን ይሠራ ይሆን?’ ብለው አሰቡ።

ከዚያም ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ። እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገረ፦ ‘ይሖዋ ይወደስ። እኛን የሚያድን መሲሕ  እንደሚልክ ለአብርሃም ቃል ገብቶለት ነበር። ዮሐንስ ነቢይ ይሆናል፤ ለመሲሑም መንገድ ያዘጋጃል።’

የኤልሳቤጥ ዘመድ የሆነችው ማርያምም አንድ ለየት ያለ ነገር አጋጠማት። ይህን በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።

“ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል።”—ማቴዎስ 19:26