በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 73

ዮሐንስ ለመሲሑ መንገድ አዘጋጀ

ዮሐንስ ለመሲሑ መንገድ አዘጋጀ

የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ልጅ የሆነው ዮሐንስ ካደገ በኋላ ነቢይ ሆነ። ይሖዋ መሲሑ እንደሚመጣ ለሰዎች እንዲናገር ዮሐንስን ላከው። ዮሐንስ ያስተማረው በምኩራቦች ወይም በከተሞች ውስጥ ሳይሆን በምድረ በዳ ነበር። ብዙ ሰዎች ዮሐንስ የሚያስተምረውን ትምህርት ለማዳመጥ ከኢየሩሳሌምና ከመላው ይሁዳ ይመጡ ነበር። አምላክን ማስደሰት ከፈለጉ መጥፎ ነገሮችን መሥራት ማቆም እንዳለባቸው ነገራቸው። አብዛኞቹ ሰዎች ዮሐንስ የሚያስተምረውን ትምህርት ከሰሙ በኋላ ከኃጢአታቸው ንስሐ ገቡ፤ ከዚያም ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ አጠመቃቸው።

ዮሐንስ ሀብት አልነበረውም። ልብሱ ከግመል ፀጉር የተሠራ ሲሆን አንበጣና የጫካ ማር ይበላ ነበር። ሰዎች ስለ ዮሐንስ ማወቅ ይፈልጉ ነበር። ኩራተኛ የሆኑት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሳይቀር እሱን ለማየት ይመጡ ነበር። ዮሐንስም እንዲህ አላቸው፦ ‘መጥፎ ሥራችሁን መተውና ንስሐ መግባት አለባችሁ። የአብርሃም ልጆች ነን ስለምትሉ ብቻ ከሌሎች ሰዎች የተሻላችሁ እንደሆናችሁ አድርጋችሁ አታስቡ። እንዲህ ስላላችሁ የአምላክ ልጆች ናችሁ ማለት አይደለም።’

ብዙ ሰዎች ወደ ዮሐንስ መጥተው ‘አምላክን ለማስደሰት ምን ማድረግ አለብን?’ ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም አይሁዳውያኑን ‘ሁለት ልብስ ካላችሁ አንዱን ለተቸገረ ሰው ስጡ’ አላቸው። ዮሐንስ እንዲህ ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አምላክን ማስደሰት ከፈለጉ ሰዎችን መውደድ እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ፈልጎ ስለነበረ ነው።

ዮሐንስ ቀረጥ ሰብሳቢዎቹን ‘ሐቀኞች ሁኑ፤ ሰዎችን አታታሉ’ አላቸው። ወታደሮቹን ደግሞ ‘ጉቦ አትቀበሉ ወይም አትዋሹ’ አላቸው።

 ካህናትና ሌዋውያንም ወደ ዮሐንስ መጥተው ‘አንተ ማን ነህ? ሁሉም ሰው ማን እንደሆንክ ማወቅ ይፈልጋል’ በማለት ጠየቁት። ዮሐንስም ‘ኢሳይያስ እንደተናገረው በምድረ በዳ ሰዎችን ስለ ይሖዋ የማስተምር ሰው ነኝ’ አላቸው።

ሕዝቡ ዮሐንስ የሚያስተምረውን ትምህርት ይወዱት ነበር። ብዙ ሰዎች ዮሐንስ መሲሕ መስሏቸው ነበር። እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘ከእኔ የሚበልጥ ይመጣል። እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም። እኔ በውኃ እያጠመቅኩ ነው፤ እሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃል።’

“ይህ ሰው ስለ ብርሃኑ ይመሠክር ዘንድ ምሥክር ሆኖ መጣ፤ ይህን ያደረገው ሁሉም ዓይነት ሰዎች በእሱ በኩል እንዲያምኑ ነው።”—ዮሐንስ 1:7