በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 60

ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር መንግሥት

ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር መንግሥት

አንድ ቀን ንጉሥ ናቡከደነጾር ተኝቶ ሳለ ለየት ያለ ሕልም አየ። ሕልሙ በጣም ስለረበሸው እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። ስለዚህ አስማተኞቹን በሙሉ አስጠራቸውና ‘ያየሁትን ሕልም ትርጉም ንገሩኝ’ አላቸው። እነሱም ‘ንጉሥ ሆይ፣ ያየኸውን ሕልም ንገረን’ አሉት። ናቡከደነጾር ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘ያየሁትን ሕልም ራሳችሁ ንገሩኝ፤ አለዚያ እገድላችኋለሁ።’ እነሱም ‘ያየኸውን ሕልም ንገረን፤ ከዚያም ትርጉሙን እንነግርሃለን’ አሉት። ንጉሡም መልሶ ‘ልታታልሉኝ እየሞከራችሁ ነው። ያየሁትን ሕልም ንገሩኝ!’ አላቸው። በዚህ ጊዜ ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ ‘ይህን ሊያደርግ የሚችል ሰው የለም። የጠየቅከው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው።’

ናቡከደነጾር በጣም ስለተናደደ በባቢሎን ያሉት አስማተኞችና ጥበበኛ ሰዎች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። ይህም ዳንኤልን፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ይጨምር ነበር። ስለዚህ ዳንኤል ትንሽ ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀ። ከዚያም እሱና ጓደኞቹ ይሖዋ እንዲረዳቸው ጸለዩ። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ?

ይሖዋ ለዳንኤል የናቡከደነጾርን ሕልምና ትርጉሙን በራእይ ገለጠለት። በቀጣዩ ቀን ዳንኤል ወደ ንጉሡ አገልጋይ ሄዶ እንዲህ አለው፦ ‘ጥበበኛ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዳቸውንም አትግደሉ። እኔ ለንጉሡ የሕልሙን ትርጉም እነግረዋለሁ።’ ከዚያም አገልጋዩ ዳንኤልን ወደ ናቡከደነጾር ወሰደው። ዳንኤልም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ ‘አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ገልጦልሃል። በሕልም ያየኸው አንድ ትልቅ ምስል ነበር፤ የምስሉ ራስ ወርቅ፣ ደረቱና እጆቹ ብር፣ ሆዱና ጭኖቹ መዳብ፣ ቅልጥሞቹ ብረት፣ እግሮቹ ደግሞ የሸክላና የብረት ቅልቅል ነበሩ። ከዚያም አንድ ድንጋይ ከተራራ ላይ ተፈነቀለና የምስሉን እግር መታው። ምስሉም ተሰባብሮ ደቀቀ፤ ነፋስም ጠራርጎ ወሰደው። ከዚያም ድንጋዩ ትልቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሁሉ ሞላ።’

ዳንኤልም እንዲህ አለ፦ ‘የሕልምህ ትርጉም ይህ ነው፦ የወርቁ ራስ የአንተ መንግሥት ነው። ብሩ ደግሞ ከአንተ  በኋላ የሚመጣን መንግሥት ያመለክታል። ከዚያም በመዳብ የተመሰለ መላውን ምድር የሚገዛ መንግሥት ይነሳል። ቀጥሎ የሚነሳው መንግሥት ደግሞ እንደ ብረት ጠንካራ ይሆናል። በመጨረሻም ግማሹ እንደ ብረት ጠንካራ፣ ግማሹ ደግሞ እንደ ሸክላ ደካማ የሆነ የተከፋፈለ መንግሥት ይነሳል። ትልቅ ተራራ የሚሆነው ድንጋይ የአምላክ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት ሁሉንም መንግሥታት ያጠፋና ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።’

ናቡከደነጾር በዳንኤል ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፋ። ከዚያም እንዲህ አለ፦ ‘ይህን ሕልም የገለጠልህ አምላካችሁ ነው። እንደ እሱ ያለ አምላክ የለም።’ ናቡከደነጾር ዳንኤልን ከመግደል ይልቅ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ አስተዳዳሪና የባቢሎን አውራጃ ገዢ አደረገው። ይሖዋ የዳንኤልን ጸሎት የመለሰለት እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ?

“እነሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።”—ራእይ 16:16