በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 59

ይሖዋን የታዘዙ አራት ልጆች

ይሖዋን የታዘዙ አራት ልጆች

ናቡከደነጾር ከንጉሡና ከመሳፍንቱ ዘር የሆኑትን አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን ከወሰዳቸው በኋላ አሽፈኔዝ የተባለውን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን በእነሱ ላይ ኃላፊ አድርጎ ሾመው። ናቡከደነጾር አሽፈኔዝን ወደ ባቢሎን ከመጡት ወጣቶች መካከል ይበልጥ ጤናማና ጎበዝ የሆኑትን እንዲመርጥ አዘዘው። እነዚህ ወጣቶች በባቢሎን ውስጥ ባለሥልጣን እንዲሆኑ ለሦስት ዓመት ያህል ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ወጣቶቹ የባቢሎንን ቋንቋ ማንበብ፣ መጻፍና መናገር እንዲችሉ መማር ነበረባቸው። እንዲሁም ንጉሡና መኳንንቱ የሚበሉትን ዓይነት ምግብ መብላት ይጠበቅባቸው ነበር። ከእነዚህ ልጆች መካከል አራቱ ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ነበሩ። አሽፈኔዝ ለእነዚህ ልጆች ብልጣሶር፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በማለት ባቢሎናውያን የሚጠሩበት ዓይነት ስም አወጣላቸው። ታዲያ እነዚህ ልጆች የባቢሎናውያንን ትምህርት መማራቸው  ይሖዋን ማምለካቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋቸው ይሆን?

እነዚህ አራት ልጆች ይሖዋን ለመታዘዝ ወስነው ነበር። የይሖዋ ሕግ የአንዳንድ እንስሳትን ሥጋ እንዳይበሉ ይከለክል ስለነበር የንጉሡን ምግብ መብላት እንደሌለባቸው ተገንዝበው ነበር። ስለዚህ አሽፈኔዝን ‘እባክህ የንጉሡን ምግብ እንድንበላ አታድርገን’ አሉት። አሽፈኔዝ ግን ‘ይህን ምግብ ሳትበሉ ቀርታችሁ ንጉሡ ከስታችሁ ቢያይ እኔን ይገድለኛል!’ አላቸው።

ዳንኤል አንድ ሐሳብ መጣለት። አሽፈኔዝን እንዲህ አለው፦ ‘እባክህ ለአሥር ቀን ያህል አትክልትና ውኃ ብቻ ስጠን። ከዚያም የንጉሡን ምግብ ከሚበሉት ልጆች ይልቅ እኛ ከስተን እንደሆነና እንዳልሆነ ታያለህ።’ አሽፈኔዝም በዚህ ሐሳብ ተስማማ።

አሥሩ ቀን ካለፈ በኋላ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ከሌሎቹ ልጆች የበለጠ ጤናማ ሆነው ተገኙ። ይሖዋም እሱን ስለታዘዙት ደስ አለው። እንዲያውም ለዳንኤል ራእዮችንና ሕልሞችን የመረዳት ችሎታ ሰጠው።

ሥልጠናቸውን ከጨረሱ በኋላ አሽፈኔዝ ልጆቹን ናቡከደነጾር ፊት አቀረባቸው። ንጉሡም ካነጋገራቸው በኋላ ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ከሌሎቹ ልጆች የበለጠ ጎበዝና አስተዋይ ሆነው አገኛቸው። ስለዚህ በቤተ መንግሥቱ እንዲያገለግሉ ሾማቸው። ንጉሡ ከበድ ያለ ጉዳይ ሲያጋጥመው ምክር ይጠይቃቸው ነበር። ይሖዋ እነዚህን ልጆች ንጉሡን ከሚያገለግሉት ጥበበኛ ሰዎችና ከአስማተኞቹ ሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ አደረጋቸው።

ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ከአገራቸው ርቀው የሚኖሩ ቢሆንም የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን አልረሱም። አንተስ ወላጆችህ አብረውህ በማይሆኑበት ጊዜም ጭምር ይሖዋን ሁልጊዜ ትታዘዛለህ?

“ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን።”—1 ጢሞቴዎስ 4:12