ከጊዜ በኋላ ቤልሻዛር የባቢሎን ንጉሥ ሆነ። አንድ ቀን ቤልሻዛር በአገሩ ላሉ አንድ ሺህ ታላላቅ ሰዎች የራት ግብዣ አዘጋጀ። ቤልሻዛር፣ ናቡከደነጾር ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን የወርቅ ዕቃዎች እንዲያመጡ አገልጋዮቹን አዘዘ። ቤልሻዛርና እንግዶቹ በወርቅ ዕቃዎቹ እየጠጡ የራሳቸውን አማልክት አወደሱ። ከዚያም በድንገት የሰው እጅ ታየና በምግብ አዳራሹ ግድግዳ ላይ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ቃላት መጻፍ ጀመረ።

በዚህ ጊዜ ቤልሻዛር በጣም ፈራ። በመሆኑም አስማተኞቹን አስጠራና ‘የእነዚህን ቃላት ትርጉም የሚነግረኝ ሰው ካለ በባቢሎን ውስጥ ሦስተኛ ገዢ እንዲሆን አደርገዋለሁ’ አላቸው። አስማተኞቹ ትርጉሙን ለመረዳት ቢሞክሩም አልቻሉም። ከዚያም ንግሥቲቱ መጣችና እንዲህ አለችው፦ ‘ለናቡከደነጾር እንቆቅልሾችንና ከባድ ነገሮችን ይፈታለት የነበረ ዳንኤል የሚባል ሰው አለ። እሱ የእነዚህን ቃላት ትርጉም ሊነግርህ ይችላል።’

በመሆኑም ዳንኤልን ንጉሡ ፊት አቀረቡት። ቤልሻዛርም እንዲህ አለው፦ ‘እነዚህን ቃላት አንብበህ ትርጉማቸውን ከነገርከኝ የወርቅ ሐብል እሰጥሃለሁ፤ እንዲሁም በባቢሎን ላይ ሦስተኛ ገዢ ትሆናለህ።’ ዳንኤልም እንዲህ አለ፦ ‘ስጦታህን አልፈልግም፤ ሆኖም የእነዚህን ቃላት ትርጉም እነግርሃለሁ። አባትህ ናቡከደነጾር ትዕቢተኛ በሆነ ጊዜ ይሖዋ አዋርዶት ነበር። አንተም በእሱ ላይ የደረሰውን ነገር በሙሉ ታውቃለህ፤ ሆኖም በቤተ መቅደሱ ዕቃዎች የወይን ጠጅ በመጠጣት ይሖዋን እንደምትንቅ አሳይተሃል። ስለዚህ አምላክ ሚኒ፣ ሚኒ፣ ቲቄል እና ፋርሲን የሚሉትን እነዚህን ቃላት አጻፈ። የእነዚህ ቃላት ትርጉም “ሜዶናውያንና ፋርሳውያን ባቢሎንን ያሸንፏታል፤ አንተም ከዚህ በኋላ ንጉሥ አትሆንም” የሚል ነው።’

በዚያ ዘመን ባቢሎንን ማሸነፍ የሚቻል አይመስልም ነበር። ምክንያቱም ከተማዋ በጠንካራ ግንብ የታጠረች ነበረች፤ እንዲሁም በዙሪያዋ የኤፍራጥስ ወንዝ ይገኝ ነበር። ሆኖም በዚያ ሌሊት ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በከተማዋ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ። የፋርሱ  ንጉሥ ቂሮስ ጥልቅ የሆነውን የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ወታደሮቹ ያለምንም ችግር ወደ ከተማዋ በሮች እንዲሄዱ አደረገ። ወደዚያ ሲደርሱ በሮቹ ክፍት ነበሩ! ወታደሮቹ ወደ ከተማዋ ገብተው ድል አደረጓት፤ ንጉሡንም ገደሉት። ከዚያም ቂሮስ የባቢሎን ገዢ ሆነ።

ቂሮስም እንዲህ በማለት አዋጅ አስነገረ፦ ‘ይሖዋ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደሱን መልሼ እንድገነባ አዞኛል። ከአምላክ ሕዝብ መካከል በግንባታው መካፈል የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ይችላል።’ በመሆኑም ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከ70 ዓመት በኋላ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ቂሮስ፣ ናቡከደነጾር ከቤተ መቅደሱ ወስዷቸው የነበሩትን የወርቅና የብር ዕቃዎች ወደ ኢየሩሳሌም መለሰ። ይሖዋ ቂሮስን በመጠቀም ሕዝቡን የረዳው እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ?

“ወደቀች! ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ . . . ሆነች!”—ራእይ 18:2