በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?

 ትምህርት 2

አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፈጠረ

አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፈጠረ

ይሖዋ ኤደን በሚባል ቦታ የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ። በአትክልት ስፍራው ውስጥ ብዙ አበቦች፣ ዛፎችና እንስሳት ነበሩ። ከዚያም አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከአፈር ሠራውና በአፍንጫው እፍ አለበት። በዚህ ጊዜ ሕይወት ያለው ሰው ሆነ! ይሖዋ አዳምን የአትክልት ስፍራውን እንዲንከባከብና ለእንስሳቱ በሙሉ ስም እንዲያወጣ ነገረው።

ይሖዋ ለአዳም አንድ አስፈላጊ መመሪያ ሰጠው። እንዲህ አለው፦ ‘በአትክልቱ ስፍራ ያሉት ዛፎች የሚያፈሩትን ፍሬ ሁሉ መብላት ትችላለህ፤ ከአንዱ ዛፍ ግን አትብላ። ከዚያ ዛፍ ከበላህ ትሞታለህ።’

ቀጥሎ ይሖዋ ‘ለአዳም ረዳት እሠራለታለሁ’ አለ። ከዚያም አዳም ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ፤ በኋላም ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዱን በመጠቀም ለአዳም ሚስት ሠራለት። የሚስቱ ስም ሔዋን ነበር። ይሖዋ የመጀመሪያውን ቤተሰብ የመሠረተው በዚህ መንገድ ነው። ይሖዋ ሔዋንን ሲፈጥርለት አዳም ምን ተሰማው? አዳም በጣም ተደስቶ እንዲህ አለ፦ ‘ይሖዋ የጎድን አጥንቴን ወስዶ ሚስት ሠራልኝ! አሁን እንደ እኔ ያለች ሰው አገኘሁ!’

 ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ልጆች እንዲወልዱና ምድርን እንዲሞሉ ነገራቸው። በተጨማሪም መላዋን ምድር በመንከባከብ ገነት ወይም ልክ እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ውብ መናፈሻ እንዲያደርጓት ፈልጎ ነበር። ግን እንደዚያ አልሆነም። ለምን? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ለዚህ ጥያቄ መልስ እናገኛለን።

“ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ [ፈጠራቸው]።”—ማቴዎስ 19:4