በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

በእምነታቸው ምሰሏቸው

 ምዕራፍ አሥራ ዘጠኝ

ቤተሰቡን ጠብቋል፣ ተንከባክቧል፣ ኃላፊነቱን ተወጥቷል

ቤተሰቡን ጠብቋል፣ ተንከባክቧል፣ ኃላፊነቱን ተወጥቷል

1, 2. (ሀ) ዮሴፍና ቤተሰቡ ሕይወታቸውን የሚለውጥ ምን ሁኔታ አጋጠማቸው? (ለ) ዮሴፍ ለባለቤቱ የትኛውን አሳዛኝ ዜና መንገር ነበረበት?

ዮሴፍ የቀረውን ጓዝ ሰብስቦ አህያው ላይ ጫነ። በጨለማ የተዋጠውን የቤተልሔም መንደር ዘወር ብሎ ከቃኘ በኋላ አህያውን ቸብ እያደረገ መጓዝ ሲጀምር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በዚህ ወቅት ወደ ግብፅ ስለሚያደርገው ረጅም ጉዞ እያሰበ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ቤተሰቡ ለአገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ እንደመሆኑ መጠን የሕዝቡ ቋንቋም ሆነ ባሕል አዲስ እንደሚሆንበት ግልጽ ነው። ታዲያ ይህ ቤተሰብ ከዚህ ሁሉ ለውጥ ጋር የሚላመደው እንዴት ነው?

2 ዮሴፍ አሳዛኙን ዜና ለውድ ባለቤቱ ለማርያም መናገር ቀላል ባይሆንለትም እንደምንም ራሱን አደፋፍሮ ነገራት። ከአምላክ የተላከ አንድ መልአክ በሕልሙ ተገልጦለት ንጉሥ ሄሮድስ ሕፃን ልጃቸውን ሊገድለው እንደሚፈልግ እንደነገረው ገለጸላት! ስለሆነም በአፋጣኝ መሸሽ ነበረባቸው። (ማቴዎስ 2:13, 14ን አንብብ።) ማርያም ሁኔታው በጣም ረብሿታል። ክፉ ደግ የማያውቀውን ልጇን ለመግደል የሚፈልግ ሰው እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ ለማርያምም ሆነ ለዮሴፍ ፈጽሞ ሊገባቸው አልቻለም። ያም ቢሆን በይሖዋ በመተማመን ለመሸሽ ተዘጋጁ።

3. ዮሴፍና ቤተሰቡ ቤተልሔምን ለቀው ሲሄዱ ስለነበረው ሁኔታ ግለጽ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 ዮሴፍ፣ ማርያምና ኢየሱስ በዚያ ጨለማ ከተማዋን ለቀው ሲወጡ የሚጠብቃቸውን ጉድ ያላወቁት የቤተልሔም ነዋሪዎች ግን አገር ሰላም ብለው ተኝተው ነበር። ከዚያም ቤተሰቡ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሲያቀና ጀምበሯ በስተ ምሥራቅ ብቅ ማለት ጀመረች፤ በዚህ ወቅት ዮሴፍ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ነገር ሳያሳስበው አይቀርም። ዝቅተኛ ኑሮ ያለው አንድ አናጺ፣ ቤተሰቡን እጅግ ኃያል ከሆኑ ጠላቶች መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው? ደግሞስ የቤተሰቡን ፍላጎት ሁልጊዜ ማሟላት ይችል ይሆን? ይህን ልዩ የሆነ ልጅ ተንከባክቦ እንዲያሳድግ ይሖዋ አምላክ የሰጠውን ከባድ ኃላፊነት በታማኝነት መወጣት ይችል ይሆን? በእርግጥም ዮሴፍ አስጨናቂ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከፊቱ ይጠብቁታል። ያጋጠሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት እንደተወጣቸው መመልከታችን በዛሬው ጊዜ ያሉ አባቶችን ጨምሮ ሁላችንም ዮሴፍን በእምነቱ መምሰል ያለብን ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል።

ዮሴፍ ቤተሰቡን ከአደጋ ጠብቋል

4, 5. (ሀ) የዮሴፍ ሕይወት እስከወዲያኛው የተለወጠው እንዴት ነበር? (ለ) ዮሴፍ የተሰጠውን ከባድ ኃላፊነት እንዲቀበል አንድ መልአክ ያበረታታው እንዴት ነው?

4 ይህ ሁሉ ከመሆኑ ከተወሰኑ ወራት በፊት፣ ዮሴፍ በሚኖርባት በናዝሬት ከተማ  ከሄሊ ልጅ ጋር ተጫጭቶ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ ሕይወቱ እስከወዲያኛው እንዲለወጥ አድርጓል። ዮሴፍ እስከሚያውቀው ድረስ ማርያም ንጹሕ እና ታማኝ ሴት ናት። ይሁን እንጂ በኋላ ላይ መጸነሷን ተገነዘበ! በዚህ ጊዜ ዮሴፍ፣ ለኀፍረት እንዳትዳረግ ሲል በስውር ሊፈታት አሰበ። * ይሁንና አንድ መልአክ በሕልም ታይቶት ማርያም የጸነሰችው በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ ገለጸለት። መልአኩ አክሎም የሚወለደው ልጅ “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” በማለት ነገረው። በተጨማሪም “እሷን ወደ ቤት ለመውሰድ አትፍራ” በማለት ዮሴፍን አበረታታው።—ማቴ. 1:18-21

5 ጻድቅና ታዛዥ የነበረው ዮሴፍ መልአኩ እንደነገረው አደረገ። ዮሴፍ በዚህ ጊዜ የተቀበለው ኃላፊነት በጣም ከባድ ነበር፤ ማርያም ያረገዘችው ልጅ የእሱ ባይሆንም እንኳ ለአምላክ እጅግ ውድ የሆነውን ይህን ልጅ ተንከባክቦ ማሳደግ ይጠበቅበት ነበር። ቆየት ብሎም ዮሴፍ የንጉሠ ነገሥቱን አዋጅ በመታዘዝ፣ ነፍሰ ጡር የነበረችውን ባለቤቱን ይዞ ለምዝገባ ወደ ቤተልሔም ሄደ። ልጁም እዚያው ተወለደ።

6-8. (ሀ) የዮሴፍንና የቤተሰቡን ሕይወት በድጋሚ የሚለውጥ ምን ነገር ተከሰተ? (ለ) ኮከቡን የላከው ሰይጣን እንደሆነ የሚጠቁም ምን ማስረጃ አለ? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

6 ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ናዝሬት አልተመለሰም። ከዚህ ይልቅ ከኢየሩሳሌም ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በቤተልሔም መኖር ጀመሩ። ዮሴፍና ማርያም ድሆች የነበሩ ቢሆንም ዮሴፍ ለማርያምና ለኢየሱስ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ እንዲሁም እነሱን ከአደጋ ለመጠበቅ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤተሰቡ በአንዲት አነስተኛ ቤት ውስጥ መኖር ጀመረ። ከዚያም ኢየሱስ አንድ ዓመት ገደማ ሲሆነው የቤተሰባቸውን ሕይወት በድንገት የሚለውጥ ነገር እንደገና አጋጠማቸው።

7 አንድ ቀን ከምሥራቅ አገር የተነሱ የተወሰኑ ኮከብ ቆጣሪዎች ወደ ዮሴፍ ቤት መጡ፤ እነዚህ ሰዎች የመጡት ርቃ ከምትገኘው ከባቢሎን ሳይሆን አይቀርም። ወደዚያም የሄዱት አንድ ኮከብ እየመራቸው ሲሆን ወደፊት የአይሁድ ንጉሥ የሚሆነውን ሕፃን ለማየት ፈልገው ነበር። ሰዎቹ ለቤተሰቡ ጥልቅ አክብሮት ነበራቸው።

8 ሆኖም እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሕፃኑን ኢየሱስን ትልቅ አደጋ ላይ ጥለውታል። እየመራ ያመጣቸው ኮከብ በመጀመሪያ የወሰዳቸው ወደ ቤተልሔም ሳይሆን ወደ ኢየሩሳሌም ነበር። * እዚያም ሲደርሱ ክፉ ለሆነው ለንጉሥ ሄሮድስ ወደፊት የአይሁድ ንጉሥ የሚሆነውን ሕፃን ለማግኘት እንደፈለጉ ገለጹለት። እሱም ይህን ሲሰማ ቅናት ስላደረበት እጅግ ተቆጣ።

9-11. (ሀ) ከሄሮድስም ሆነ ከሰይጣን የሚበልጥ ኃይል ያላቸው አካላት ምን አድርገው ነበር? (ለ) ቤተሰቡ ወደ ግብፅ ያደረገው ጉዞ የአዋልድ ተረቶችና አፈ ታሪኮች ከሚናገሩት የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

9 ደግነቱ ከሄሮድስም ሆነ ከሰይጣን የሚበልጥ ኃይል ያላቸው አካላት አሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስ ወደነበረበት ቤት ደርሰው ሕፃኑንና እናቱን ሲያዩ በምላሹ ምንም እንዲደረግላቸው ሳይጠብቁ ለቤተሰቡ ስጦታዎችን ሰጡ። ዮሴፍና ማርያም እንደ “ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ” ያሉ ውድ ነገሮችን በድንገት ሲያገኙ ምንኛ ተገርመው ይሆን! ኮከብ ቆጣሪዎቹ ሲፈልጉት የነበረውን ሕፃን የት እንዳገኙት  ለንጉሥ ሄሮድስ ሊነግሩት አስበው ነበር። ሆኖም በዚህ ጊዜ ይሖዋ ጣልቃ ገባ። ኮከብ ቆጣሪዎቹ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱም በሕልም አማካኝነት አዘዛቸው።—ማቴዎስ 2:1-12ን አንብብ።

10 ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከሄዱ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ መልአክ ዮሴፍን እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ፈልጎ ሊገድለው ስላሰበ ተነስ፣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤ እኔ እስካሳውቅህም ድረስ እዚያው ቆይ።” (ማቴ. 2:13) ስለዚህ በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንዳየነው ዮሴፍ የታዘዘውን በመስማት አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። ከምንም ነገር በላይ የልጁን ደህንነት በማስቀደም ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ። እነዚያ አረማውያን ኮከብ ቆጣሪዎች ለቤተሰቡ ውድ ስጦታዎች ስለሰጧቸው ዮሴፍ ወደ ግብፅ ለመጓዝም ሆነ በዚያ ለመኖር የሚያስችል በቂ ሀብት አግኝቶ ነበር።

ዮሴፍ ልጁን ከአደጋ ለመጠበቅ ቆራጥና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ እርምጃ ወስዷል

11 ከጊዜ በኋላ የአዋልድ ተረቶችና አፈ ታሪኮች ወደ ግብፅ የተደረገውን ጉዞ አዛብተው በማቅረብ ሕፃኑ ኢየሱስ በተአምር ጉዞውን እንዳሳጠረው፣ ሽፍቶች ጉዳት እንዳያደርሱባቸው እንዳደረገ አልፎ ተርፎም የተምር ዛፎች ዘንበል እንዲሉ በማድረግ እናቱ ፍሬዎቹን እንድትለቅም እንዳስቻላት ይናገራሉ። * እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ቤተሰቡ ወደዚያ ባዕድ አገር ያደረገው ጉዞ ረጅምና አድካሚ ነበር።

ዮሴፍ ለቤተሰቡ ሲል የግል ምቾቱን መሥዋዕት አድርጓል

12. በዚህ አደገኛ ዓለም ውስጥ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ወላጆች ከዮሴፍ ምን ሊማሩ ይችላሉ?

12 ወላጆች ከዮሴፍ ሊማሩ የሚችሉት ብዙ ነገር አለ። ዮሴፍ ቤተሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል ያላንዳች ማንገራገር ሥራውን ትቷል እንዲሁም የግል ምቾቱን መሥዋዕት አድርጓል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቤተሰቡን ከይሖዋ እንደተሰጠው ውድ ስጦታ አድርጎ ተመልክቶታል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ልጆችን ለአደጋ የሚያጋልጥ፣ አእምሯቸውን የሚበክል አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን የሚያበላሽ ተጽዕኖ ባየለበት አደገኛ ዓለም ውስጥ ነው። ልጆቻቸውን እንዲህ ካሉ አደጋዎች ለመጠበቅ ልክ እንደ ዮሴፍ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉና ቆራጥ እርምጃ የሚወስዱ እናቶችና አባቶች ሊደነቁ ይገባል!

ዮሴፍ ቤተሰቡን ተንከባክቧል

13, 14. ዮሴፍና ማርያም ልጆቻቸውን ለማሳደግ ተመልሰው ወደ ናዝሬት የሄዱት ለምንድን ነው?

13 ቤተሰቡ ወደ ግብፅ ከሄደ ብዙም ሳይቆይ መልአኩ፣ ሄሮድስ መሞቱን ለዮሴፍ ስለነገረው በግብፅ የቆየበት ጊዜ ያን ያህል ረጅም አይመስልም። በመሆኑም ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ። አንድ ጥንታዊ ትንቢት ይሖዋ፣ ልጁን “ከግብፅ” እንደሚጠራው ይናገራል። (ማቴ. 2:15) ዮሴፍ ይህ ትንቢት እንዲፈጸም አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ይሁንና ይህ ቤተሰብ አሁን የት ሊኖር ነው?

14 ዮሴፍ ጠንቃቃ ሰው ነበር። ሄሮድስን ተክቶ የነገሠው አርኬላዎስም ልክ እንደ አባቱ ጨካኝና ነፍሰ ገዳይ በመሆኑ ዮሴፍ እሱን መፍራቱ ተገቢ ነበር። አምላክ በሰጠው  መመሪያ መሠረት ዮሴፍ ከኢየሩሳሌምና በዚያ ሊያጋጥመው ከሚችለው አደጋ ለመራቅ በስተ ሰሜን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ቤተሰቡን ይዞ ሄደ። እሱና ማርያም ልጆቻቸውን ያሳደጉት በዚያ ነው።—ማቴዎስ 2:19-23ን አንብብ።

15, 16. ዮሴፍ የሚሠራው ሥራ ምን ነገሮችን ያጠቃልል ነበር? ምን ዓይነት መሣሪያዎችንስ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል?

15 ዮሴፍና ማርያም ቀለል ያለ ሕይወት ይመሩ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነበር ማለት ግን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ አናጺ እንደነበረ ይናገራል፤ አናጺ ተብሎ የተተረጎመው ቃል፣ ዮሴፍ ከእንጨት ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን ያከናውን እንደነበር ያመለክታል፤ ይህም ዛፍ መቁረጥንና ማጓጓዝን ከዚያም እንጨቱን አድርቆ በማስተካከል ቤቶችን፣ ጀልባዎችን፣ አነስተኛ ድልድዮችን፣ ጋሪዎችን፣ የእንጨት ጎማዎችን፣ ቀንበሮችንና ማንኛውንም ዓይነት የእርሻ መሣሪያዎችን መሥራትን ይጨምራል። (ማቴ. 13:55) አናጺነት ከባድ የጉልበት ሥራ ይጠይቅ ነበር። በጥንት ዘመን የነበሩ አናጺዎች ብዙውን ጊዜ የሚሠሩት ትንሽ በሆነው ቤታቸው ደጃፍ ላይ አሊያም ከቤታቸው አጠገብ ባለ ክፍል ውስጥ ነበር።

16 ዮሴፍ የተለያዩ መሣሪያዎችን ይጠቀም የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹ ከአባቱ የወረሳቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። ምናልባትም ስኳድራ፣ ቱንቢ፣ ጠመኔ፣ መጥረቢያ፣ መጋዝ፣ ፋስ፣ የብረት መዶሻ፣ የእንጨት መዶሻ፣ መሮዎች፣ በደጋን የሚሠራ መሰርሰሪያ፣ የተለያዩ ዓይነት ማጣበቂያዎች እንዲሁም ዋጋቸው ውድ ቢሆንም ምስማሮች ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል።

17, 18. (ሀ) ኢየሱስ ከአሳዳጊ አባቱ ምን ነገሮችን ተምሯል? (ለ) ዮሴፍ ይበልጥ ጠንክሮ መሥራት የነበረበት ለምንድን ነው?

17 ኢየሱስ ልጅ በነበረበት ወቅት አሳዳጊ አባቱ የሚሠራውን በንቃት ሲከታተል በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ዓይኖቹን በዮሴፍ ላይ ተክሎ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ሲመለከት በአባቱ የፈረጠመ ጡንቻ፣ ጠንካራ ክንዶችና በእጆቹ ቅልጥፍና እንዲሁም በብልሃት በሚያከናውነው ሥራ እንደሚደነቅ ጥርጥር የለውም። ምናልባትም ዮሴፍ፣ የደረቀ የዓሣ ቆዳ በመጠቀም እንጨትን እንደ ማለስለስ ያሉ ቀላል ሥራዎችን እንዴት መሥራት እንደሚቻል ለልጁ ሳያሳየው አልቀረም። ከዚህም ሌላ የተለያየ ነገር ለመሥራት በሚጠቀምባቸው እንጨቶች ለአብነት ያህል በሾላ፣ በኦክ ወይም በወይራ ዛፍ መካከል ያለውን ልዩነት ለኢየሱስ አስተምሮት ሊሆን ይችላል።

ዮሴፍ ልጁን አናጺ እንዲሆን አሠልጥኖታል

18 በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ዮሴፍ በፈረጠሙ ክንዶቹ ዛፎችን መቁረጥ፣ ትላልቅ ግንዶችን ፈልጦ ማዘጋጀት ብሎም አንድ ላይ አገጣጥሞ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መሥራት የሚችል ጠንካራ ሰው ብቻ ሳይሆን እናቱንም ሆነ እሱንና ታናናሾቹን እቅፍ አድርጎ  የሚያበረታታና የሚያጽናና ርኅሩኅ አባት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ የዮሴፍና የማርያም ቤተሰብ እየሰፋ የሄደ ሲሆን ከኢየሱስ ሌላ ቢያንስ ስድስት ልጆች ነበሯቸው። (ማቴ. 13:55, 56) ዮሴፍ እነዚህን ሁሉ ልጆች ተንከባክቦ ለማሳደግ ይበልጥ ጠንክሮ መሥራት ነበረበት።

ዮሴፍ ተቀዳሚው ኃላፊነቱ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደሆነ ያውቅ ነበር

19. ዮሴፍ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ምን ያደርግ ነበር?

19 ይሁን እንጂ ዮሴፍ ተቀዳሚው ኃላፊነቱ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደሆነ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ጊዜ መድቦ ልጆቹን ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ሕጎቹ ያስተምራቸው ነበር። እሱና ማርያም ልጆቻቸውን ሕጉ ከፍ ባለ ድምፅ እየተነበበ ወደሚብራራበት በአካባቢው ወደሚገኝ ምኩራብ አዘውትረው ይወስዷቸው ነበር። ከምኩራብ ሲመለሱ በኢየሱስ አእምሮ ውስጥ በርካታ ጥያቄዎች ሳይፈጠሩ አይቀርም፤ ዮሴፍም የልጁን መንፈሳዊ ጥማት ለማርካት የተቻለውን ሁሉ አድርጎ መሆን አለበት። በተጨማሪም ዮሴፍ ቤተሰቡን በኢየሩሳሌም ወደሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት ይዞ ይሄድ ነበር። ዮሴፍና ቤተሰቡ በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው የማለፍ በዓል ላይ ለመገኘትና ወደ ቤታቸው ለመመለስ ሁለት ሳምንት ገደማ የሚፈጅባቸው ሲሆን 120 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሸፍን ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር።

ዮሴፍ ይሖዋን ለማምለክ ቤተሰቡን ይዞ በኢየሩሳሌም ይገኝ ወደነበረው ቤተ መቅደስ ዘወትር ይሄድ ነበር

20. ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶች የዮሴፍን አርዓያ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

20 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያደርጋሉ። እነዚህ ወላጆች ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ያላቸውን ነገር ሁሉ ለልጆቻቸው ይሰጣሉ፤ ሆኖም ቁሳዊ ነገሮችን ጨምሮ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ልጆቻቸውን በመንፈሳዊ ማሠልጠን እንደሆነ ይገነዘባሉ። የቤተሰብ አምልኮን ለመምራትም ሆነ ልጆቻቸውን ወደ ሳምንታዊ ስብሰባዎችና ወደ ትላልቅ ስብሰባዎች ለመውሰድ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። ልክ እንደ ዮሴፍ እነዚህም ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያደርጉላቸው ከሚችሉት ነገር ሁሉ እጅግ የላቀው እነሱን ስለ ይሖዋ ማስተማር እንደሆነ ያውቃሉ።

‘በጣም ተጨንቀን ነበር’

21. የዮሴፍ ቤተሰብ የማለፍን በዓል የሚያሳልፈው እንዴት ነበር? ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ አብሯቸው አለመሆኑን የተገነዘቡት መቼ ነበር?

21 ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ዮሴፍ እንደተለመደው ቤተሰቡን ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ ሄደ። አስደሳች በሆነው በዚህ የማለፍ በዓል ወቅት በርካታ ቤተሰቦች በጸደይ ልምላሜ የተዋቡትን ገጠራማ አካባቢዎች እያቋረጡ አንድ ላይ ይጓዛሉ። ብዙዎቹ አይሁዳውያን ከፍ ብላ በምትታየው በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወደሚገኘው ገላጣ ስፍራ ሲደርሱ ተወዳጅ የሆኑትን የመዓርግ (ወደ ላይ የመውጣት) መዝሙሮች ይዘምሩ ነበር። (መዝ. 120 እስከ 134) ከተማዋ በመቶ ሺህዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ሳትጥለቀለቅ አትቀርም። ከበዓሉ በኋላ፣ ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ወደ ቤታቸው መመለስ ጀመሩ። ምናልባትም በወቅቱ ተዋክበው የነበሩት ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ ከዘመዶቻቸው ጋር እየተጓዘ ያለ ሳይመስላቸው አይቀርም። ኢየሱስ አብሯቸው አለመሆኑን የተገነዘቡት  ከኢየሩሳሌም ወጥተው የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዙ በኋላ ነበር፤ በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጡ!—ሉቃስ 2:41-44

22, 23. ዮሴፍና ማርያም ልጃቸው መጥፋቱን በተገነዘቡ ጊዜ ምን አደረጉ? ልጃቸውን ሲያገኙትስ ማርያም ምን አለችው?

22 ዮሴፍና ማርያም በጭንቀት ተውጠው እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በዚህ ወቅት ከተማዋ ጭር ያለች ሆና እንደምትታያቸው ልትገምት ትችላለህ፤ እዚያ እንደደረሱም በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ ልጃቸውን እየተጣሩ ወዲያና ወዲህ ሲሉ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ልጁ የት ገብቶ ይሆን? ለሦስት ቀናት ፈልገው ሲያጡት ዮሴፍ ከይሖዋ የተቀበለውን ቅዱስ አደራ እንዳልጠበቀ ማሰብ ጀምሮ ይሆን? በመጨረሻም ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱ። ቤተ መቅደሱን ሲያስሱ ከቆዩ በኋላ በሕጉ የተካኑ ብዙ ምሁራን ወደተሰበሰቡበት አንድ ክፍል መጡ፤ በዚያም ኢየሱስን በመካከላቸው ተቀምጦ  አዩት! በዚህ ጊዜ ዮሴፍና ማርያም ምን ያህል እፎይታ እንደተሰማቸው አስብ!—ሉቃስ 2:45, 46

23 ኢየሱስ ምሁራኑን እያዳመጣቸው እንዲሁም የማወቅ ጉጉት ስለነበረው ጥያቄዎችን እየጠየቃቸው ነበር። ሰዎቹም በልጁ ማስተዋልና በመልሶቹ ተደንቀው ነበር። ማርያምና ዮሴፍ ግን በጣም ደንግጠዋል። ዘገባው ዮሴፍ የተናገረው ነገር እንዳለ አይገልጽም። ማርያም የተናገረችው ልብ የሚነካ ሐሳብ ግን የሁለቱንም ስሜት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል፤ “ልጄ፣ ምነው እንዲህ አደረግከን? እኔና አባትህ እኮ በጣም ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።—ሉቃስ 2:47, 48

24. መጽሐፍ ቅዱስ ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ጥሩ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?

24 በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈረው ይህ አጭር ዘገባ ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ፍጹም ልጅ ማሳደግ እንኳ ውጥረት ሊፈጥር  ይችላል! አደገኛ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ወላጅ መሆን ይህ ነው የማይባል ‘ጭንቀት’ ሊያስከትል ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚገልጽ መሆኑ ወላጆችን ሊያጽናናቸው ይችላል።

25, 26. ኢየሱስ ለወላጆቹ ምን መልስ ሰጣቸው? ዮሴፍ ኢየሱስ የተናገረውን ሲሰማ ምን ዓይነት ስሜት ሳያድርበት አይቀርም?

25 ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ያገኙት በዓለም ላይ ከየትኛውም ቦታ ይበልጥ በሰማይ ወዳለው አባቱ ወደ ይሖዋ በጣም እንደቀረበ እንዲሰማው በሚያደርግ ስፍራ ሲሆን በዚያም የቻለውን ያህል እውቀት ለመቅሰም እየጣረ ነበር። በመሆኑም ለወላጆቹ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” በማለት ቅንነት የሚንጸባረቅበት መልስ ሰጣቸው።—ሉቃስ 2:49

26 ዮሴፍ ስለ እነዚህ ቃላት ደጋግሞ ያስብ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ምናልባትም ኢየሱስ የተናገረውን ሲሰማ ልቡ በኩራት ተሞልቶ ሊሆን ይችላል። ደግሞም በአደራ የተሰጠውን ልጁን ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርበት ለማድረግ በትጋት ሲያስተምረው ኖሯል። ኢየሱስ ገና በዚህ ለጋ ዕድሜው አፍቃሪ አባት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ያውቅ የነበረ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርበት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ከዮሴፍ ጋር የነበረው ግንኙነት እንደሆነ ግልጽ ነው።

27. አባት እንደመሆንህ መጠን ምን መብት አግኝተሃል? የዮሴፍን ምሳሌ ማስታወስ ያለብህስ ለምንድን ነው?

27 አንተም አባት ከሆንክ ልጆችህ አፍቃሪና ተንከባካቢ አባት ምን ዓይነት እንደሆነ እንዲያውቁ የመርዳት ትልቅ መብት እንዳለህ ትገነዘባለህ? እንዲሁም የእንጀራ ልጆች ወይም የማደጎ ልጆች ካሉህ ዮሴፍ የተወውን ምሳሌ በማስታወስ እያንዳንዱን ልጅ ልዩና ውድ እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። ልጆችህን በሰማይ ወዳለው አባታቸው፣ ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲቀርቡ እርዳቸው።—ኤፌሶን 6:4ን አንብብ።

ዮሴፍ ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል

28, 29. (ሀ) በ⁠ሉቃስ 2:51, 52 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ ዮሴፍ ምን ይገልጻል? (ለ) ዮሴፍ ልጁ በጥበብ እያደገ እንዲሄድ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል?

28 መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በኋላ ስለ ዮሴፍ የሚናገረው ነገር ጥቂት ቢሆንም እነዚህን ሐሳቦች በጥልቀት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ወላጆቹን “ይታዘዛቸው” እንደነበር ይገልጻል። በተጨማሪም  “በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ [እንደሄደ]” ይናገራል። (ሉቃስ 2:51, 52ን አንብብ።) እነዚህ ሐሳቦች ስለ ዮሴፍ የሚጠቁሙት ነገር ይኖራል? እንዴታ! ፍጹም የነበረው ልጁ የዮሴፍን ሥልጣን እንደሚያከብርና ለሥልጣኑም እንደሚገዛ መገለጹ ዮሴፍ ቤተሰቡን በኃላፊነት ማስተዳደሩን እንደቀጠለ እንድንገነዘብ ያስችለናል።

29 ኢየሱስ በጥበብም እያደገ እንደሄደ ተገልጿል። በዚህ ረገድ ዮሴፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚያ ዘመን አይሁዶች ታዋቂ የሆነ አንድ ጥንታዊ አባባል ነበራቸው። በዛሬው ጊዜም ይህን አባባል ከመጽሐፎቻቸው ላይ ማንበብ ይቻላል። አባባሉ ጥበበኛ መሆን የሚችሉት ዘና ያለ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የሚናገር ሲሆን እንደ አናጺ፣ ገበሬና አንጥረኛ የመሳሰሉት የእጅ ሞያተኞች ግን “ስለ ፍትሕና ስለ ፍርድ መናገር አይችሉም፤ እንዲሁም ምሳሌዎች በሚነገሩበት ቦታ መገኘት የለባቸውም” ይላል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ይህ አባባል ትክክል እንዳልሆነ አጋልጧል። አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ ዝቅተኛ ኑሮ የሚመራ አናጺ የነበረ ቢሆንም ስለ ይሖዋ “ፍትሕና ፍርድ” ጥሩ አድርጎ ሲያስተምር ኢየሱስ ልጅ እያለ በተደጋጋሚ ሰምቶት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!

30. ዮሴፍ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ የቤተሰብ ራሶች ምሳሌ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?

30 ዮሴፍ፣ ኢየሱስ በአካል እያደገ እንዲሄድም አስተዋጽኦ እንዳደረገ የሚያሳይ ማስረጃ እናገኛለን። ኢየሱስ በልጅነቱ ጥሩ እንክብካቤ በማግኘቱ ጠንካራና ጤነኛ ሰው ሊሆን ችሏል። ከዚህም ሌላ ዮሴፍ ልጁን በሙያው የተካነ እንዲሆን አሠልጥኖታል። ኢየሱስ የአናጺው ልጅ ብቻ ሳይሆን “አናጺው” በመባልም ይታወቅ ነበር። (ማር. 6:3) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ዮሴፍ የሰጠው ሥልጠና ውጤታማ ነበር። የቤተሰብ ራሶች፣ ልጆቻቸው ጤናማ ሆነው እንዲያድጉና ራሳቸውን ችለው ለመኖር የሚያስችላቸውን ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ዮሴፍን መምሰላቸው የጥበብ እርምጃ ነው።

31. (ሀ) ዮሴፍ የሞተው መቼ እንደሆነ የሚጠቁም ምን ማስረጃ አለ? (ሣጥኑንም ተመልከት።) (ለ) ዮሴፍ ልንከተለው የሚገባ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

31 ኢየሱስ በ30 ዓመቱ እንደተጠመቀ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በኋላ ስለ ዮሴፍ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ማስረጃው እንደሚጠቁመው ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት ማርያም መበለት ነበረች። (“ዮሴፍ የሞተው መቼ ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) ሆኖም ዮሴፍ ቤተሰቡን ከአደጋ በመጠበቅ፣ በመንከባከብና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ኃላፊነቱን በታማኝነት በመወጣት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆን አባት እንደነበር የሚያሳይ አሻራ ትቶ አልፏል። ማንኛውም አባት፣ ማንኛውም የቤተሰብ ራስ አልፎ ተርፎም ማንኛውም ክርስቲያን ዮሴፍን በእምነቱ ሊመስለው ይገባል።

^ አን.4 በዚያ ዘመን፣ የተጫጩ ሰዎች የተጋቡ ያህል ተደርገው ይታዩ ነበር።

^ አን.8 ይህ ኮከብ ተፈጥሯዊ ክስተት ወይም አምላክ የላከው አልነበረም። ፍጹም እንግዳ የሆነውን ይህን ትዕይንት ሰይጣን ኢየሱስን ለማጥፋት የጠነሰሰውን ሴራ ለማሳካት እንደተጠቀመበት ምንም ጥርጥር የለውም።

^ አን.11 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የመጀመሪያውን ተአምር ይኸውም ‘ከምልክቶቹ የመጀመሪያውን’ የፈጸመው ከተጠመቀ በኋላ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል።—ዮሐ. 2:1-11