1, 2. ከኖኅ ዘመን በኋላ ዓለም የተለወጠው በምን መንገድ ነው? አብራምስ ምን ይሰማው ነበር?

አብራም ቀና ብሎ ሲመለከት ትኩረቱ፣ በሚኖርባት በዑር ከተማ ውስጥ ጉብ ብሎ በሚታየው የከለዳውያን ቤተ መቅደስ ላይ አረፈ። * በዚያም ከፍተኛ ሁካታ የሚሰማ ሲሆን ጭሱ እየተትጎለጎለ ሲወጣም ይታያል። የጨረቃ አምላክ ካህናት እንደ ልማዳቸው መሥዋዕት እያቀረቡ ነው። አብራም ግንባሩን አኮሳትሮ ራሱን በመነቅነቅ ፊቱን ሲያዞር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በሰው የተጨናነቁትን ጎዳናዎች አቋርጦ ወደ ቤቱ ሲሄድ በዑር ከተማ ስለተንሰራፋው የጣዖት አምልኮ ሳያስብ አይቀርም። ብልሹ የሆነው ይህ አምልኮ ከኖኅ ዘመን አንስቶ በዓለም ላይ ሲስፋፋ ቆይቷል።

2 ኖኅ የሞተው አብራም ከመወለዱ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው በኋላ ከመርከብ ሲወጡ ኖኅ ለይሖዋ አምላክ መሥዋዕት አቅርቦ የነበረ ሲሆን ይሖዋም ቀስተ ደመና እንዲታይ አድርጓል። (ዘፍ. 8:20፤ 9:12-14) በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ከንጹሕ አምልኮ በቀር ሌላ አምልኮ አልነበረም። ከኖኅ በኋላ የመጣው አሥረኛ ትውልድ በምድር ላይ ወደተለያየ አካባቢ ሲበተን ግን ንጹሕ አምልኮ ብርቅ እየሆነ ሄደ። በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች ባዕድ አማልክትን ያመልኩ ነበር። ሌላው ቀርቶ የአብራም አባት የሆነው ታራ በጣዖት አምልኮ ይካፈል ነበር፤ ምናልባትም ጣዖታትን ሳይሠራ አይቀርም።—ኢያሱ 24:2

አብራም እምነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ እንደሆነ ተደርጎ የሚጠቀሰው ለምንድን ነው?

3. ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አብራምን ከሌሎች ተለይቶ እንዲታወቅ ያደረገው የትኛው ባሕርይው ነው? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?

3 አብራም በአካባቢው ካሉት ሰዎች የተለየ ነበር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ደግሞ በእምነቱ የተነሳ ከሌሎች የተለየ መሆኑ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ በመንፈስ ተመርቶ ‘የሚያምኑ ሁሉ አባት’ ሲል ጠርቶታል። (ሮም 4:11ን አንብብ።) አብራም እንዲህ ዓይነት ሰው ሊሆን የበቃው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። እግረ መንገዳችንንም እምነታችን እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።

 ከጥፋት ውኃ በኋላ ባለው ዓለም ውስጥ ይሖዋን ማገልገል

4, 5. አብራም ስለ ይሖዋ ያወቀው ከማን ሊሆን ይችላል? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?

4 አብራም ስለ ይሖዋ አምላክ ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? በዚያ ዘመን ይሖዋ በምድር ላይ ታማኝ አገልጋዮች እንደነበሩት እናውቃለን። ከእነዚህ መካከል አንዱ ሴም ነበር። ምንም እንኳ ሴም ከሦስቱ የኖኅ ወንዶች ልጆች መካከል በኩር ባይሆንም ብዙውን ጊዜ መጀመሪያ ላይ የሚጠቀሰው እሱ ነው። ይህም የሆነው ሴም በእምነቱ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ሰው ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። * የጥፋት ውኃ ከተከሰተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኖኅ ይሖዋን “የሴም አምላክ” ሲል ጠርቶታል። (ዘፍ. 9:26) ሴም ለይሖዋና ለንጹሕ አምልኮ አክብሮት እንደነበረው አሳይቷል።

5 አብራም ሴምን ያውቀው ነበር? ያውቀዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። እስቲ አብራም በልጅነት ዕድሜው ላይ እንዳለ አድርገህ አስብ። አብራም ከአራት ዘመናት በላይ የሰው ልጅ ታሪክ ሲቀያየር ያየውና ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው ቅድመ አያቱ በሕይወት እንዳለ ሲያውቅ በጣም ተደንቆ መሆን አለበት! ሴም ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዓለም ይፈጸም የነበረውን ክፋት፣ ምድርን ያጸዳውን ታላቅ የጥፋት ውኃ፣ የሰው ልጆች በምድር ላይ እየበዙ በመሄዳቸው የተነሳ የተቋቋሙትን የመጀመሪያዎቹን ብሔራት እንዲሁም በባቤል ግንብ ይኖር የነበረው ናምሩድ ያመፀበትን የጨለማ ዘመን ተመልክቷል። ታማኙ ሴም በዚያ ዓመፅ አልተካፈለም፤ በመሆኑም ይሖዋ የባቤልን ግንብ ይገነቡ የነበሩትን ሰዎች ቋንቋ ባደባለቀበት ወቅት ሴምና ቤተሰቡ የሰው ልጆች የመጀመሪያ ቋንቋ የሆነውን የኖኅን ቋንቋ መናገራቸውን ቀጥለዋል። አብራምም የዚህ ቤተሰብ አባል ነበር። ስለሆነም አብራም ከልጅነቱ ጀምሮ ለሴም ትልቅ አክብሮት እንደነበረው ግልጽ ነው። አልፎ ተርፎም በአብዛኛው የአብራም የሕይወት ዘመን ሴምም በሕይወት ነበር። ስለዚህ አብራም ስለ ይሖዋ ያወቀው ከሴም ሊሆን ይችላል።

አብራም ዑርን ካጥለቀለቀው የጣዖት አምልኮ ርቋል

6. (ሀ) አብራም ተከስቶ ከነበረው የጥፋት ውኃ ትምህርት እንዳገኘ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) አብራምና ሦራ ምን ዓይነት ሕይወት ይመሩ ነበር?

6 ያም ሆነ ይህ አብራም በኖኅ ዘመን ተከስቶ ከነበረው የጥፋት ውኃ ትልቅ ትምህርት አግኝቷል። ኖኅ ከአምላክ ጋር እንደሄደ ሁሉ እሱም ከአምላክ ጋር ለመሄድ ጥረት አድርጓል። አብራም ከጣዖት አምልኮ የራቀውና በዑር ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች ምናልባትም ከቅርብ የቤተሰቡ አባላት ሳይቀር የተለየ ሊሆን የቻለው በዚህ ምክንያት ነው። ያም ሆኖ ግሩም የሆነች የሕይወት አጋር አግኝቷል። በውበቷ ብቻ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ባላት ጠንካራ እምነት ተለይታ የምትታወቀውን ሦራን አገባ። * እነዚህ ባልና  ሚስት ልጅ ያልነበራቸው ቢሆንም አብረው ይሖዋን በማገልገል ይደሰቱ እንደነበር ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም ወላጆቹን በሞት ያጣውንና የአብራም ወንድም ልጅ የሆነውን ሎጥን ያሳድጉ ነበር።

7. የኢየሱስ ተከታዮች አብራም የተወውን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

7 አብራም በዑር በነበረው የጣዖት አምልኮ ተማርኮ ከይሖዋ አልራቀም። እሱም ሆነ ሦራ ጣዖት አምላኪ ከሆነው ማኅበረሰብ የተለዩ ሆነው ለመኖር ፈቃደኞች ነበሩ። እኛም ጠንካራ እምነት ማዳበር ከፈለግን ተመሳሳይ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። ከሌሎች የተለየን ሆነን ለመኖር ፈቃደኞች መሆን አለብን። ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑና’ በዚህም የተነሳ ዓለም እንደሚጠላቸው ገልጿል። (ዮሐንስ 15:19ን አንብብ።) የቤተሰብህ አባላት ወይም የምትኖርበት ማኅበረሰብ አምላክን ለማገልገል በመምረጥህ የተነሳ ስላገለሉህ አዝነህ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰብህ አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አስታውስ። አብራምና ሦራ እንዳደረጉት ሁሉ አንተም ከአምላክ ጋር እየሄድክ ነው ማለት ነው።

‘ከአገርህ ተለይተህ ሂድ’

8, 9. (ሀ) አብራም ምን የማይረሳ ነገር ገጠመው? (ለ) ይሖዋ ለአብራም የነገረው መልእክት ምንድን ነው?

8 አንድ ቀን አብራም ፈጽሞ የማይረሳ ነገር ገጠመው። ከይሖዋ አምላክ የመጣ አንድ ልዩ መልእክት ተቀበለ! መጽሐፍ ቅዱስ አብራም ይህን መልእክት የተቀበለው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ባይገልጽም “የክብር አምላክ” ለዚህ ታማኝ አገልጋይ እንደተገለጠለት ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 7:2, 3ን አንብብ።) ምናልባትም አብራም የአምላክ ወኪል በሆነ አንድ መልአክ አማካኝነት የጽንፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ አስደናቂ ክብር በጥቂቱ ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። አብራም ሕያው በሆነው አምላክና በአካባቢው ያሉት ሰዎች በሚያመልኳቸው በድን ጣዖታት መካከል ያለውን ልዩነት ሲመለከት ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

9 ይሖዋ ለአብራም የነገረው መልእክት ምንድን ነው? “ከአገርህና ከዘመዶችህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ” አለው። ይሖዋ ለአብራም የሚሄድበትን ምድር እንደሚያሳየው ገለጸለት እንጂ እንዲሄድ ያሰበው ወደ የትኛው ምድር እንደሆነ በግልጽ አልነገረውም። ይሁን እንጂ አብራም በቅድሚያ አገሩንና ወዳጅ ዘመዶቹን ትቶ መውጣት ነበረበት። በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ የነበረው ባሕል ለቤተሰብ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። አንድ ሰው ከወዳጅ ዘመዶቹ ተለይቶ ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ከተገደደ መጥፎ ዕድል እንደገጠመው ተደርጎ ይታሰብ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ከሞት እንኳ የከፋ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር!

10. አብራምና ሦራ በዑር የነበረውን መኖሪያቸውን ለቀው መሄዳቸው መሥዋዕትነት ጠይቆባቸው ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

10 አብራም አገሩን ለቆ መሄዱ መሥዋዕትነት ጠይቆበታል። ዑር የደራችና የበለጸገች ከተማ እንደነበረች አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። (“ አብራምና ሦራ ትተዋት የወጡት ከተማ” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) በመሬት ቁፋሮ የተገኙ ማስረጃዎች በጥንቷ የዑር ከተማ በጣም ምቹ የሆኑ ቤቶች እንደነበሩ ያሳያሉ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ቤቶች ለቤተሰቡ አባላትና ለአገልጋዮቻቸው የሚሆኑ 12ና ከዚያ  በላይ ክፍሎች የነበራቸው ሲሆን ግቢያቸውም በድንጋይ የተነጠፈ ነበር። እንዲሁም ኅብረተሰቡ በጋራ የሚገለገልባቸው የውኃ መሥመሮች፣ መጸዳጃ ቤቶችና የቆሻሻ ማስወገጃዎች ነበሩ። በዚህ ወቅት አብራምና ሦራ ወጣት እንዳልነበሩ አስታውስ፤ ምናልባትም አብራም በ70ዎቹ፣ ሦራ ደግሞ በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሳይሆኑ አይቀሩም። አብራም ማንኛውም ጥሩ ባል ለሚስቱ እንደሚመኘው ሁሉ እሱም በተቻለ መጠን ሦራ ተመችቷትና ጥሩ እንክብካቤ አግኝታ እንድትኖር እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። እነዚህ ባልና ሚስት የተሰጣቸውን ትእዛዝ አስመልክቶ በአእምሯቸው ውስጥ ተነስተው ሊሆኑ የሚችሉ ጥያቄዎችንና ያሳሰቧቸውን ነገሮች አንስተው ሲወያዩ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ሦራ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆኗ አብራምን በጣም አስደስቶት መሆን አለበት! ሦራ ልክ እንደ ባሏ የምቾት ኑሮዋን ትታ ለመሄድ ፈቃደኛ ነበረች።

11, 12. (ሀ) አብራምና ሦራ ዑርን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ምን ዝግጅትና ውሳኔ ማድረግ ነበረባቸው? (ለ) ጉዞ በጀመሩበት ዕለት የነበረውን ሁኔታ እንዴት አድርገን ልንገልጸው እንችላለን?

11 አብራምና ሦራ ይህን ውሳኔ ከወሰኑ በኋላ ከፊታቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ጓዛቸውን መሸከፉና አንዳንድ ነገሮችን ማደራጀቱ ቀላል ሥራ አይደለም። ወደማያውቁት ስፍራ ለመጓዝ ሲነሱ የትኞቹን ነገሮች መያዝና የትኞቹን ነገሮች መተው ይኖርባቸው ይሆን? ይሁን እንጂ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው አብረዋቸው የሚኖሩት ሰዎች ጉዳይ ነው። በዕድሜ የገፋውን ታራን በተመለከተስ ምን ቢያደርጉ ይሻላል? ታራን ይዘውት ለመሄድና ለመጦር ወሰኑ። ዘገባው ታራ ቤተሰቡን ይዞ ከዑር እንደወጣ አድርጎ ስለሚገልጽ እሱም ያለማቅማማት በሐሳባቸው ተስማምቶ መሆን አለበት። ጣዖት ማምለኩን ትቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የአብራም የወንድሙ ልጅ የሆነው ሎጥም ከተጓዦቹ መካከል አንዱ ነበር።—ዘፍ. 11:31

12 በመጨረሻም ጉዟቸውን የሚጀምሩበት ቀን ደረሰ። ለጉዞ የተዘጋጁ ሰዎችና ጓዝ የጫኑ እንስሳት ከዑር ከተማ ቅጥር ውጪ ቆመው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ግመሎቹና አህዮቹ ዕቃ ተጭነዋል፤ መንጋዎቹ አንድ ላይ ተሰብስበዋል፤ የቤተሰቡ አባላትና አገልጋዮቹም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፤ ሁሉም ጉዟቸውን ለመጀመር ጓጉተዋል። * ምናልባትም አብራም ጉዞ እንዲጀምሩ እስኪነግራቸው እየተጠባበቁ ሊሆን ይችላል። አሁን በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ጊዜ ደረሰ፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዑርን ለቀው መጓዝ ጀመሩ።

13. በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች የአብራምና የሦራ ዓይነት መንፈስ ያሳዩት እንዴት ነው?

13 በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ተጨማሪ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረው ለማገልገል ወስነዋል። ሌሎች ደግሞ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ ሌላ ቋንቋ ተምረዋል። ወይም ቀደም ሲል ተጠቅመውበት የማያውቁትን የስብከት ዘዴ ለመሞከር ጥረት አድርገዋል። በጥቅሉ ሲታይ እንዲህ ያሉትን እርምጃዎች መውሰድ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ምቾትን መሥዋዕት ማድረግ  እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። አብራምና ሦራ የተዉትን ምሳሌ በመከተል እንዲህ ዓይነቱን መንፈስ ማሳየት በእርግጥም የሚያስመሰግን ነው! እንዲህ ያለ እምነት እንዳለን የምናሳይ ከሆነ ይሖዋ እኛ ከሰጠነው ይበልጥ አትረፍርፎ እንደሚባርከን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ይሖዋ እምነት ላሳዩ ሰዎች ወሮታ ከመክፈል ወደኋላ ብሎ አያውቅም። (ዕብ. 6:10፤ 11:6) ታዲያ ለአብራም ወሮታ ከፍሎታል?

ኤፍራጥስን ተሻገሩ

14, 15. አብራምና ቤተሰቡ ከዑር ወደ ካራን ያደረጉት ጉዞ ምን ይመስል ነበር? አብራም በካራን ለተወሰነ ጊዜ ለመቆየት የወሰነው ለምን ሊሆን ይችላል?

14 ተጓዦቹ ቀስ በቀስ ጉዞውን እየተለማመዱት መጡ። አብራምና ሦራ በእንስሳቱ አንገት ላይ በተንጠለጠለው ቃጭል ድምፅ ታጅበው እርስ በርስ እየተጨዋወቱ አንዴ በእንስሳ ላይ ተቀምጠው ሲጓዙ፣ ከዚያ ደግሞ ወርደው በእግራቸው ሲሄዱ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የጉዞ ልምድ የሌላቸው ተጓዦችም እንኳ በጊዜ ሂደት ድንኳን መትከልንና ነቅሎ መጓዝን እንዲሁም በዕድሜ የገፋውን ታራን ግመል ወይም አህያ ላይ ተመቻችቶ እንዲቀመጥ መርዳትን ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር ይበልጥ እየተለማመዱ ሄደዋል። ተጓዦቹ የኤፍራጥስን ወንዝ ተከትለው ወደ ሰሜን ምዕራብ አቀኑ። ቀናት ሳምንታትን እየወለዱ ሜዳ ሸንተረሩን አቋርጠው ገሰገሱ።

15 በመጨረሻም 960 ኪሎ ሜትር ገደማ ከተጓዙ በኋላ በካራን ወደሚገኙት ጎጆዎች ደረሱ፤ ካራን ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚያቀኑ የንግድ መሥመሮች አቋርጠዋት የሚያልፉ የበለጸገች ከተማ ነበረች። ተጓዦቹም በዚያ ለተወሰነ ጊዜ ቆዩ።  ምናልባትም ይህን ያደረጉት ታራ ከዚያ በላይ የመጓዝ አቅም ስላልነበረው ሊሆን ይችላል።

16, 17. (ሀ) አብራምን እንዲበረታታ ያደረገው የትኛው ቃል ኪዳን ነው? (ለ) አብራም በካራን በቆየበት ጊዜ ይሖዋ የባረከው እንዴት ነው?

16 በኋላም ታራ በ205 ዓመቱ ሞተ። (ዘፍ. 11:32) በዚህ ጊዜ ይሖዋ አብራምን በድጋሚ ስላነጋገረው አብራም ከደረሰበት ሐዘን ተጽናንቷል። ይሖዋ፣ አብራም በዑር ሳለ የሰጠውን መመሪያ በድጋሚ የነገረው ሲሆን ቀደም ሲል የገባለትንም ቃል በስፋት ገልጾለታል። በመሆኑም አብራም “ታላቅ ሕዝብ” ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በእሱ የተነሳ በረከት የሚያገኙበት አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል። (ዘፍጥረት 12:2, 3ን አንብብ።) አምላክ በገባለት በዚህ ቃል ኪዳን በጣም የተበረታታው አብራም ጉዞውን መቀጠል እንዳለበት ተሰምቶት ነበር።

17 አብራም በካራን በቆየበት ጊዜ ይሖዋ ባርኮት ስለነበር ጉዞውን ለመቀጠል ሲነሳ ከበፊቱ የበለጠ ብዙ ጓዝ መሸከፍ ነበረበት። ዘገባው “በካራን ሳሉ ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዘው” እንደተጓዙ ይገልጻል። (ዘፍ. 12:5) አብራም ታላቅ ሕዝብ እንዲሆን ከተፈለገ ብዙ ቁሳዊ ሀብትና አገልጋዮች ያሉት ትልቅ ቤተሰብ ሊኖረው ይገባል። ይሖዋ ሁልጊዜ አገልጋዮቹን ባለጸጋ ያደርጋቸዋል ማለት ባይሆንም ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ማንኛውንም ነገር ይሰጣቸዋል። በዚህ መንገድ የተበረታታው አብራም ጓዙን ይዞ ወደማያውቀው አገር መጓዙን ቀጠለ።

አብራምና ሦራ በዑር የነበራቸውን የተመቻቸ ኑሮ ትተው መሄዳቸው ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች ይዳርጋቸው ነበር

18. (ሀ) አምላክ ከሕዝቡ ጋር በነበረው ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የተከፈተው መቼ ነው? (ለ) ቆየት ብሎ ባሉት ዓመታት በኒሳን 14 ምን ሌሎች ጉልህ ክንውኖች ተፈጽመዋል? (“ በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዕለት” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

18 ከካራን ተነስቶ ብዙውን ጊዜ መንገደኞች የኤፍራጥስን ወንዝ ወደሚሻገሩበት ወደ ካርከሚሽ መድረስ ለበርካታ ቀናት መጓዝ ይጠይቃል። አምላክ ከሕዝቡ ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተው አብራም እዚህ ቦታ ላይ በደረሰበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው አብራምና ቤተሰቡ የኤፍራጥስን ወንዝ የተሻገሩት በ1943 ዓ.ዓ. በኒሳን ወር (ይህ ወር ኒሳን ተብሎ የተሰየመው ከጊዜ በኋላ ነው) በ14ኛው ቀን ነው። (ዘፀ. 12:40-43) ይሖዋ ለአብራም ሊያሳየው ቃል የገባለት ምድር በስተ ደቡብ ተንጣሎ ይታያል። በዚያ ቀን አምላክ ለአብራም የገባለት ቃል ኪዳን ሥራ ላይ መዋል ጀመረ።

19. ይሖዋ ለአብራም የገባለት ቃል ስለ ምን ነገር ይጠቅሳል? ይህስ አብራምን ምን ነገር አስታውሶት ሊሆን ይችላል?

19 አብራምና ቤተሰቡ በስተ ደቡብ ምድሩን አቋርጠው ሲጓዙ ከቆዩ በኋላ በሴኬም አቅራቢያ ያሉት  የሞሬ ትላልቅ ዛፎች ጋ ሲደርሱ አረፍ አሉ። አሁንም አብራም በዚያ ከይሖዋ መልእክት ተቀበለ። በዚህ ጊዜ አምላክ ለአብራም የገባለት ቃል ምድሪቱን ስለሚወርሰው የአብራም ዘር ይጠቅሳል። ታዲያ አብራም ይህን ሲሰማ ይሖዋ ወደፊት የሰውን ዘር የሚታደገውን “ዘር” አስመልክቶ በኤደን የተናገረውን ትንቢት አስታውሶ ይሆን? (ዘፍ. 3:15፤ 12:7) ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ሊፈጽመው ባሰበው ታላቅ ዓላማ ውስጥ አብራም ራሱ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ግን እምብዛም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

20. አብራም ይሖዋ ለሰጠው መብት አድናቆት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

20 አብራም ይሖዋ ለሰጠው መብት ጥልቅ አድናቆት ነበረው። ምድሪቱን አቋርጦ ሲሄድ አብራም በመጀመሪያ በሞሬ ትላልቅ ዛፎች አጠገብ በኋላም በቤቴል አቅራቢያ ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤ ከነዓናውያን ገና ከምድሪቱ ላይ ስላልተባረሩ አብራም የሚጓዘው በጥንቃቄ እንደነበር ጥርጥር የለውም። አብራም የይሖዋን ስም መጥራቱ ስለ ዘሩ የወደፊት ሁኔታ ሲያሰላስል ያደረበትን ልባዊ አድናቆት ለአምላኩ መግለጹን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ለከነዓናውያን ጎረቤቶቹ ሰብኮ ይሆናል። (ዘፍጥረት 12:7, 8ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ አብራም እምነቱን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ገና ከፊቱ ይጠብቁታል። አብራም በዑር ትቶት የወጣውን ቤትና እዚያ የነበረውን የምቾት ኑሮ በማሰብ አልተቆጨም። ከዚህ ይልቅ ትኩረቱ ያረፈው ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ ነበር። ዕብራውያን 11:10 አብራምን አስመልክቶ ሲናገር “አምላክ የገነባትንና የሠራትን እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር” ይላል።

21. ከአብራም ጋር ሲነጻጸር የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ያለን ግንዛቤ ምን ይመስላል? ይህስ ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

21 በዛሬው ጊዜ የምንገኘው የይሖዋ አገልጋዮች ስለዚያች ምሳሌያዊ ከተማ ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት ከአብራም የተሻለ እውቀት አለን። ይህ መንግሥት በሰማይ በመግዛት ላይ እንደሚገኝና ይህን ክፉ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚያጠፋው እንዲሁም ለረጅም ጊዜ በተስፋ ሲጠበቅ የቆየው የአብራም ዘር ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግሥት ንጉሥ መሆኑን እናውቃለን። አብራም ትንሣኤ አግኝቶ ስለ ይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም የተሟላ ግንዛቤ ሲያገኝ መመልከት ለእኛ ትልቅ መብት ነው! ይሖዋ የገባቸው ተስፋዎች በሙሉ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ መመልከት ትፈልጋለህ? ከሆነ በተቻለ መጠን አብራም እንዳደረገው ማድረግህን ቀጥል። የራስን ጥቅም የመሠዋትና የታዛዥነት መንፈስ አሳይ፤ እንዲሁም ይሖዋ ለሰጠህ መብቶች ልባዊ አድናቆት ይኑርህ። ‘ለሚያምኑ ሁሉ አባት’ የሆነው አብራም እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ የምትከተል ከሆነ አብራም ለአንተም አባትህ ይሆናል!

^ አን.1 ከጊዜ በኋላ አምላክ የአብራምን ስም አብርሃም ብሎ የቀየረው ሲሆን ትርጉሙም “የብዙ ሕዝቦች አባት” ማለት ነው።—ዘፍ. 17:5

^ አን.4 በተመሳሳይም አብራም የበኩር ልጅ ባይሆንም ከታራ ወንዶች ልጆች መካከል ብዙውን ጊዜ መጀመሪያ ላይ የሚጠቀሰው እሱ ነው።

^ አን.6 ከጊዜ በኋላ አምላክ የሦራን ስም ሣራ ብሎ የቀየረው ሲሆን ትርጉሙም “ልዕልት” ማለት ነው።—ዘፍ. 17:15

^ አን.12 አንዳንድ ምሁራን በአብራም ዘመን ሰዎች ግመልን ማላመድ ስለመቻላቸው ጥያቄ ያነሳሉ። ሆኖም ይህ የተቃውሞ ሐሳብ መሠረተ ቢስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብራም ንብረቶች ሲገልጽ ግመሎችን በተደጋጋሚ ጊዜ ይጠቅሳል።—ዘፍ. 12:16፤ 24:35