በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

እውነተኛ እምነት ደስታ ያስገኝልሃል

 ክፍል 12

እውነተኛ እምነት እንዳለህ አሳይ!

እውነተኛ እምነት እንዳለህ አሳይ!

አምላክ፣ አገልጋዮቹ የእምነት ፈተና ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል። ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።” (1 ጴጥሮስ 5:⁠8) ሰይጣን እምነትህን ለማጥፋት የሚሞክረው እንዴት ነው?

እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ አጋጥሞህ ያውቃል?

ሰይጣን ቅዱሳን መጻሕፍትን መመርመር እንድትተው ጫና ለማሳደር ሌሎችን እንዲያውም ቤተሰብህንና ወዳጅ ዘመዶችህን ሊጠቀም ይችላል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ (ኢሳ) “በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:​36) የቤተሰብህ አባላትና ጓደኞችህ በቅንነት የሚቃወሙህ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ድንቅ እውነቶች ስለማያውቁ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ‘ሰዎች ምን ይሉኛል’ የሚለው ነገር አስፈርቷቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በይሖዋ የሚታመን ግን ጥበቃ ያገኛል” ይላሉ። (ምሳሌ 29:​25) ሰዎችን ለማስደሰት ብለህ ቅዱሳን መጻሕፍትን መማርህን ብታቆም አምላክ ደስ ይለዋል? ደስ እንደማይለው የታወቀ ነው! በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ እምነት የምናሳይ ከሆነ አምላክ ይረዳናል። “እኛ በሕይወት የሚያኖር እምነት እንዳላቸው ሰዎች ነን እንጂ ወደ ጥፋት እንደሚያፈገፍጉ ሰዎች አይደለንም።”​—⁠ዕብራውያን 10:​39

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዱማስ ምን አጋጥሞት እንደነበረ አስታውስ። መጀመሪያ ላይ ሚስቱ በእምነቱ ታሾፍበት ነበር። በኋላ ግን እሷም የአምላክን ቃል አብራው መማር ጀመረች። አንተም በተመሳሳይ ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ ከጸናህ ቤተሰቦችህ እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶችህ የአንተን መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ። ብዙ የሕይወት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት አማኝ ያልነበሩ ሰዎች፣ እውነተኛ እምነት ያለው የቤተሰባቸው አባል የሚያሳየውን ‘ንጹሕ ምግባርና ጥልቅ አክብሮት’ በመመልከት ‘ያለ ቃል ተማርከዋል።’​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​1, 2

በተጨማሪም ሰይጣን፣ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥናት ጊዜ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ ይጥራል። ሰይጣን፣ በኑሮ ጫናዎች ተጠቅሞ ‘ቃሉን በማነቅ’ ሥር እንዳይሰድ ሊያደርገው ይችላል፤ በሌላ አባባል በግልህ የሚያጋጥሙህ አስጨናቂ ነገሮች እንዲሁም ገንዘብ ለማግኘት የምታደርገው ሩጫ እምነትህ “የማያፈራ” እንዲሆን ያደርጉታል። (ማርቆስ 4:​19) እንዲህ ያለው አርቆ አስተዋይነት የጎደለው አስተሳሰብ በአንተ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ተጠንቀቅ! ቅዱሳን መጻሕፍት “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” በማለት ይናገራሉ። (ዮሐንስ 17:⁠3) አዎ፣ በገነት ውስጥ ለዘላለም  መኖር ከፈለግህ ስለ አምላክና መሲሕ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ የበለጠ ለማወቅ ጥረት ማድረግህ አስፈላጊ ነው!

አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ

በግብፅ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ስለነበሩት ስለ ሙሴ (ሙሳ) አስብ። ሙሴ ሀብት፣ ዝናና ሥልጣን የማግኘት አጋጣሚ ነበራቸው። ሆኖም ሙሴ “በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን” መረጡ። ለምን? ‘የማይታየውን አምላክ እንደሚያዩት አድርገው በጽናት ስለቀጠሉ ነው።’ (ዕብራውያን 11:​24, 25, 27) ሙሴ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ነበራቸው። ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ የአምላክን ፍላጎት አስቀድመዋል፤ በዚህም የተነሳ አምላክ በእጅጉ ባርኳቸዋል። አንተም ተመሳሳይ ነገር የምታደርግ ከሆነ አምላክ ይባርክሃል።

ሰይጣን በተለያዩ መንገዶች ሊያጠምድህ ይሞክር ይሆናል። ይሁን እንጂ በወጥመዱ ውስጥ እንዳትገባ ተጠንቀቅ። የአምላክ ቃል ‘ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል’ በማለት አጥብቆ ይመክረናል። (ያዕቆብ 4:⁠7) ታዲያ ዲያብሎስን መቃወም የምትችለው እንዴት ነው?

ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናትህን ቀጥል። የአምላክን ቃል በየዕለቱ አንብብ። በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች አጥና። እንዲሁም ምክሮቹን በሥራ ላይ አውል። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የሰይጣንን ጥቃቶች ለመመከት የሚያስችለው ‘ከአምላክ የሚገኘው ሙሉ የጦር ትጥቅ’ ይኖርሃል።​—⁠ኤፌሶን 6:​13

እውነተኛ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ተቀራረብ። ቅዱሳን መጻሕፍትን የሚያነቡ፣ የሚያጠኑና በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎችን ፈልግ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ‘እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንዲችሉ አንዳቸው ለሌላው ትኩረት የሚሰጡ ከመሆኑም ሌላ እርስ በርስ ይበረታታሉ።’ ከእነሱ ጋር መቀራረብህ እምነትህ እየተጠናከረ እንዲሄድ ይረዳሃል።​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

እውነተኛ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ተቀራረብ

ከይሖዋ ጋር ተቀራረብ። ወደ አምላክ ጸልይ፤ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ይኑርህ። አምላክ ሊረዳህ እንደሚፈልግ ፈጽሞ አትርሳ። ‘አምላክ ስለ አንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣል።’ (1 ጴጥሮስ 5:​6, 7) ‘አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብህ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችል ፈተና ሲደርስብህ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልሃል።’​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​13

ሰይጣን ማንኛውም ሰው ችግር ካጋጠመው አምላክን ማገልገሉን እንደሚያቆም በመናገር አምላክን ይሳደባል። ይሁን እንጂ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል አጋጣሚ አለህ! አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።” (ምሳሌ 27:​11) አዎ፣ እውነተኛ እምነት እንዳለህ ለማሳየት ቆራጥ አቋም ውሰድ!