በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

እውነተኛ እምነት ደስታ ያስገኝልሃል

 ክፍል 2

እውነተኛ እምነት ምንድን ነው?

እውነተኛ እምነት ምንድን ነው?

እምነት እንደ ገንዘብ ነው፤ ዋጋ የሚኖረው እውነተኛ ሲሆን ነው

እውነተኛ እምነት ማዳበር አምላክ መኖሩን ከማመን የበለጠ ነገር ይጠይቃል። አምላክ መኖሩን የሚያምኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ፤ ይሁንና ሆን ብለው ክፉ ድርጊት ይፈጽማሉ። እንዲህ ዓይነቱ “እምነት” ከሐሰተኛ ገንዘብ ጋር ይመሳሰላል። ከላይ ሲታይ እውነተኛ ቢመስልም ምንም ዋጋ የለውም። ታዲያ እውነተኛ እምነት ምንድን ነው?

እውነተኛ እምነት በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኝ ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ነው። ፈጣሪ ያስጻፈው ይህ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ አምላክ እውነቱን ስለሚነግረን እሱን እንድናውቀው ያስችለናል። የእሱን ሕጎች፣ ዓላማዎችና ትምህርቶች ይገልጽልናል። ከትምህርቶቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • አምላክ አንድ ነው። አቻ የለውም።

  • ኢየሱስ (ኢሳ) ሁሉን ቻይ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ነቢይ ነው።

  • አምላክ ሁሉንም ዓይነት ጣዖት አምልኮ ያወግዛል።

  • ሰዎች ወደፊት የፍርድ ቀን ይጠብቃቸዋል።

  • ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በገነት ውስጥ ይኖራሉ።

እውነተኛ እምነት መልካም ሥራዎችን እንድንሠራ ይገፋፋናል። እንዲህ ዓይነቶቹ መልካም ሥራዎች አምላክን የሚያስከብሩ ከመሆኑም ሌላ እኛንም ሆነ ሌሎችን ይጠቅማሉ። ከእነዚህ መልካም ሥራዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • አምላክን ማምለክ።

  • አምላክ የሚወዳቸውን ባሕርያት በተለይም ፍቅርን ማዳበር።

  • ክፉ ሐሳቦችንና ምኞቶችን እርግፍ አድርጎ መተው።

  • ችግሮች ቢያጋጥሙም በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ጠብቆ መኖር።

  • ሌሎችን ስለ አምላክ ማስተማር።

እውነተኛ እምነት መልካም ሥራዎችን እንድንሠራ ይገፋፋናል

 እውነተኛ እምነት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

እምነት እንደ ጡንቻ ነው፤ ባሠራነው ቁጥር እየዳበረ ይሄዳል

አምላክ እንዲረዳህ ጠይቅ። ነቢዩ ሙሴ (ሙሳ) “እንዳውቅህና በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንድኖር መንገድህን አሳውቀኝ” በማለት ወደ አምላክ ጸልየው ነበር። * አምላክም ጸሎታቸውን ሰምቶ መልስ ሰጥቷቸዋል። ነቢዩ ሙሴ እምነት በማሳየት ረገድ ድንቅ ምሳሌ ሆነዋል። አምላክ አንተንም ቢሆን እውነተኛ እምነት እንድታዳብር ይረዳሃል።

ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥናት ጊዜ መድብ። የኦሪት፣ የመዝሙር እና የወንጌል መጻሕፍትን (ተውራት፣ ዘቡርና ኢንጅል) ጨምሮ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ቅዱሳን መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፤ ይህ መጽሐፍ በዓለም ላይ በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎምና በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። ይህ ቅዱስ መጽሐፍ አለህ? ከሌለህ፣ ይህን መጽሐፍ ለማግኘት ለምን አትሞክርም?

ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን ምክር በሕይወትህ ተግባራዊ አድርግ። እምነት ከጡንቻ ጋር ይመሳሰላል። ጡንቻህን ባሠራኸው ቁጥር እየዳበረ እንደሚሄድ ሁሉ እምነትህም በተግባር የሚገለጽ ከሆነ እየዳበረ ይሄዳል። የአምላክ ምክር ጠቃሚ እንደሆነ በራስህ ሕይወት ትመለከታለህ። ደግሞም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ጠቃሚ ምክሮች የብዙ ሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል አድርገዋል። ይህን ብሮሹር ማንበብህን ስትቀጥል ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ታገኛለህ።