በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ክፍል 11

በዛሬው ጊዜ እውነተኛ እምነት ማሳየት

በዛሬው ጊዜ እውነተኛ እምነት ማሳየት

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። እውነተኛ እምነት የሚኖራቸው ግን ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ኢየሱስ (ኢሳ) አስተምሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”​—⁠ማቴዎስ 7:​13, 14

ታዲያ በዛሬው ጊዜ እውነተኛ እምነት ያላቸውን ሰዎች ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል። “ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።” (ማቴዎስ 7:​16, 17) በመሆኑም እውነተኛ እምነት “መልካም ፍሬ” ያፈራል። በሌላ አባባል እውነተኛ እምነት፣ ሰዎች አምላክ የሚወዳቸውን ባሕርያት እንዲያፈሩ ይገፋፋል። ታዲያ እነዚህን ባሕርያት የሚያሳዩት እንዴት ነው?

ኃይላቸውን አላግባብ አይጠቀሙበትም

እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን የሚጠቀሙት አምላክን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ነው። ኢየሱስ “ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል” በማለት አስተምሯል። (ማርቆስ 10:​43) በመሆኑም እውነተኛ እምነት ያላቸው ወንዶች በቤታቸውም ሆነ ከቤታቸው ውጭ አምባገነን አይሆኑም። ለሚስቶቻቸው ፍቅርና አክብሮት አላቸው፤ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር በደስታ ያሟሉላቸዋል። ቅዱሳን መጻሕፍት “ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ መራራ ቁጣም አትቆጧቸው” ይላሉ። (ቆላስይስ 3:​19) በተጨማሪም እንዲህ በማለት ይመክራሉ፦ “እናንተ ባሎች ከእነሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ። እነሱም ከእናንተ ጋር የሕይወትን ጸጋ አብረው ስለሚወርሱ ጸሎታችሁ እንዳይታገድ ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው።”​—⁠1 ጴጥሮስ 3:7

በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ እምነት ያላት አንዲት ሚስት ‘ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።’ (ኤፌሶን 5:​33) ሚስቶች “ባሎቻቸውን የሚወዱ” እና “ልጆቻቸውን የሚወዱ” መሆን ይገባቸዋል። (ቲቶ 2:⁠4) እውነተኛ እምነት ያላቸው አባቶችና እናቶች ከልጆቻቸው ጋር አብረው ጊዜ ያሳልፋሉ፤ እንዲሁም የአምላክን ሕግና መመሪያዎች ያስተምሯቸዋል። በቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ እንዲሁም የትም ቦታ ሌሎችን ያከብራሉ። በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የሚገኘውን “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” የሚለውን ምክር ይከተላሉ።​—⁠ሮም 12:​10

የአምላክ አገልጋዮች በቅዱስ ቃሉ ላይ የሚገኘውን “ጉቦ አትቀበል” የሚለውን ትእዛዝ ያከብራሉ። (ዘፀአት 23:⁠8) ሥልጣናቸውን ለራሳቸው ጥቅም አያውሉትም። ከዚህ ይልቅ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሌሎችን በተለይ ደግሞ የተቸገሩትን ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና” የሚለውን ምክር በጥብቅ ይከተላሉ። (ዕብራውያን 13:​16) በመሆኑም ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን በራሳቸው ሕይወት መመልከት ችለዋል።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 20:​35

የአምላክን የፍትሕ መሥፈርት ይከተላሉ

እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች የአምላክን ሕጎች በፈቃደኝነት የሚታዘዙ ሲሆን ‘ትእዛዛቱ ከባድ’ እንደሆኑ አይሰማቸውም። (1 ዮሐንስ  5:⁠3) ምክንያቱም የሚከተለው ጥቅስ እውነት እንደሆነ ያምናሉ፦ “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው፤ . . . የይሖዋ መመሪያዎች ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ የይሖዋ ትእዛዝ ንጹሕ ነው፤ ዓይንን ያበራል።”​—⁠መዝሙር 19:​7, 8

በተጨማሪም እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ጭፍን ጥላቻን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳሉ። አንድን ዘር ወይም አገር ከሌላው አያበላልጡም፤ እንዲሁም ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ተመልክተው አያዳሉም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን ምሳሌ ይከተላሉ። “አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”​—⁠የሐዋርያት ሥራ 10:​34, 35

እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ‘በሁሉም ነገር ሐቀኞች ለመሆን’ ጥረት ያደርጋሉ። (ዕብራውያን 13:​18) በተጨማሪም ሐሜት ከማውራትና ስም ከማጥፋት ይቆጠባሉ። መዝሙራዊው ዳዊት (ዳውድ)፣ አምላክ ሞገሱን የሚሰጠውን ሰው አስመልክተው ሲናገሩ “በአንደበቱ ስም አያጠፋም፤ በባልንጀራው ላይ መጥፎ ነገር አይሠራም” በማለት ጽፈዋል።​—⁠መዝሙር 15:3

በአምላክ ጥበብ ይመራሉ

እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች የሚያምኑባቸው ነገሮች የተመሠረቱት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ብቻ ነው። “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ” የሚለው ጥቅስ እውነት እንደሆነ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) ከሌሎች ጋር ባላቸው ዝምድና ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ ያንጸባርቃሉ፤ ይህ ጥበብ ‘ንጹሕ፣ ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት’ ነው። (ያዕቆብ 3:​17) አምላክ ከማይወዳቸው ወጎችና መናፍስታዊ ድርጊቶች እንዲሁም ‘ከጣዖቶች ይርቃሉ።’​—⁠1 ዮሐንስ 5:​21

እውነተኛ ፍቅር ያሳያሉ

ነቢዩ ሙሴ (ሙሳ) “አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” ብለዋል። (ዘዳግም 6:⁠5) እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ለአምላክ እንዲህ ዓይነት ፍቅር አላቸው። ይሖዋ የሚለውን ስሙን ያከብራሉ። ‘ይሖዋን የሚያመሰግኑ’ ከመሆኑም ሌላ በእምነት ‘ስሙን ይጠራሉ።’ (መዝሙር 105:⁠1) በተጨማሪም የአምላክ አገልጋዮች “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ትእዛዝ ያከብራሉ። (ዘሌዋውያን 19:​18) ከዓመፅ ድርጊቶች የሚርቁ ሲሆን “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ጥረት ያደርጋሉ። (ሮም 12:​18) በምሳሌያዊ አነጋገር “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ።” (ኢሳይያስ 2:⁠4) በዚህም የተነሳ ‘እርስ በርሳቸው ፍቅር’ አላቸው፤ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር መመሥረት ችለዋል። (ዮሐንስ 13:​35) ታዲያ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለ ባሕርይ የሚያንጸባርቁትን ሰዎች ለይተህ ማወቅ ትችላለህ?