በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

 ምዕራፍ 126

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው

ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲያዝ ሐዋርያቱ ስለፈሩ ጥለውት ሸሹ። ሁለቱ ግን መሸሻቸውን አቁመው ተመለሱ። እነዚህ ሐዋርያት “ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር” እንደሆኑ ዘገባው ይገልጻል፤ ይህ ደቀ መዝሙር ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (ዮሐንስ 18:15፤ 19:35፤ 21:24) ምናልባትም ኢየሱስ ወደ ሐና ቤት እየተወሰደ ሳለ ሳይደርሱበት አልቀሩም። ሐና፣ ኢየሱስን ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ሲልከው ጴጥሮስና ዮሐንስ በርቀት ተከተሉት። በአንድ በኩል ለራሳቸው ሕይወት በመፍራት በሌላ በኩል ደግሞ ጌታቸው ስለሚደርስበት ነገር በመጨነቅ ልባቸው ለሁለት የተከፈለ ይመስላል።

ዮሐንስ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ስለሚታወቅ ወደ ቀያፋ ግቢ መግባት ቻለ። ጴጥሮስ ግን ውጭ በር ላይ ቆመ፤ ከዚያም ዮሐንስ ተመልሶ በር ጠባቂዋን አነጋገራትና ጴጥሮስን አስገባው።

ሌሊቱ ቀዝቃዛ በመሆኑ በግቢው ውስጥ ያሉት ሰዎች ከሰል አቀጣጥለዋል። ጴጥሮስ ከሰዎቹ ጋር ተቀምጦ እሳት እየሞቀ የኢየሱስን ፍርድ ‘መጨረሻ ለማየት’ እየተጠባበቀ ነው። (ማቴዎስ 26:58) በዚህ ጊዜ፣ ጴጥሮስን ያስገባችው በር ጠባቂ በእሳቱ ብርሃን በደንብ ተመለከተችው። ከዚያም “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ ነህ አይደል?” በማለት አፋጠጠችው። (ዮሐንስ 18:17) ጴጥሮስን ያወቀችውና ከኢየሱስ ጋር እንደነበረ የተናገረችው ይህቺ ሴት ብቻ አይደለችም።—ማቴዎስ 26:69, 71-73፤ ማርቆስ 14:70

ይህ ጴጥሮስን በጣም አስደነገጠው። ማንነቱ እንዳይታወቅ ለማድረግ ሞክሯል፤ እንዲያውም ወደ ግቢው መግቢያ አካባቢ ሄዷል። ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር መሆኑን ካደ፤ አልፎ ተርፎም “ሰውየውን አላውቀውም፤ ምን እንደምታወሪም አላውቅም” አለ። (ማርቆስ 14:67, 68) በተጨማሪም “ይምልና ራሱን ይረግም” ማለትም የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን በመሃላ ለማረጋገጥ ዝግጁ እንደሆነ፣ ካልሆነ ደግሞ የሚመጣበትን እርግማን እንደሚቀበል ይገልጽ ጀመር።—ማቴዎስ 26:74

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢየሱስን ጉዳይ ችሎቱ እየተመለከተው ነው፤ ችሎቱ የሚካሄደው በቀያፋ ግቢ ውስጥ ከፍ ብሎ በሚገኝ ቤት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ጴጥሮስና ሌሎች ሰዎች ከታች ሆነው ሲጠብቁ፣ ምሥክርነት ለመስጠት የሚገቡትንና የሚወጡትን የተለያዩ ሰዎች ይመለከቱ ይሆናል።

ጴጥሮስ የገሊላ ሰው መሆኑ ከአነጋገሩ ያስታውቃል፤ ስለዚህ ኢየሱስን እንደማያውቀው መናገሩ እውነት አለመሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህም ሌላ በአካባቢው ከቆሙት መካከል አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው የማልኮስ ዘመድ ነው። በመሆኑም ሰውየው “በአትክልቱ ስፍራ ከእሱ ጋር አይቼህ አልነበረም?” አለው። ጴጥሮስ ኢየሱስን ለሦስተኛ ጊዜ ሲክድ አስቀድሞ እንደተነገረው ዶሮ ጮኸ።—ዮሐንስ 13:38፤ 18:26, 27

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ግቢውን መመልከት ወደሚያስችል በረንዳ ወጣ ያለ ይመስላል። ጌታ ዞር ብሎ ጴጥሮስን ትክ ብሎ አየው፤ በዚህ ወቅት ጴጥሮስ በጣም ተሰምቶት መሆን አለበት። ሰገነት ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ እያሉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ኢየሱስ የተናገረው ነገር ትዝ አለው። ጴጥሮስ የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲገነዘብ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን አስበው! በመሆኑም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።—ሉቃስ 22:61, 62

ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በመንፈሳዊ ጠንካራና ለጌታው ታማኝ እንደሆነ በጣም እርግጠኛ የነበረው ጴጥሮስ ጌታውን ሊክድ የቻለው እንዴት ነው? እውነት እየተዛባ ነው፤ ኢየሱስም እንደ ከባድ ወንጀለኛ ተቆጥሯል። ጴጥሮስ ንጹሕ የሆነን ሰው ደግፎ መቆም ባይከብደውም “የዘላለም ሕይወት ቃል” ላለው ሰው ጀርባውን ሰጠ።—ዮሐንስ 6:68

ጴጥሮስ ላይ የደረሰው የሚያሳዝን ገጠመኝ፣ ጠንካራ እምነት ያለውና ለአምላክ ያደረ ሰው እንኳ ሊያጋጥመው ለሚችለው መከራ ወይም ፈተና ራሱን በሚገባ ካላዘጋጀ ሚዛኑን ሊስት እንደሚችል ያሳያል። ጴጥሮስ ያጋጠመው ነገር ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆናል!