በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 107

ንጉሡ ታዳሚዎችን ወደ ሠርግ ድግስ ጠራ

ንጉሡ ታዳሚዎችን ወደ ሠርግ ድግስ ጠራ

ማቴዎስ 22:1-14

  • የሠርጉ ድግስ ምሳሌ

ኢየሱስ፣ አገልግሎቱ እየተገባደደ ባለበት በዚህ ወቅት ጸሐፍትንና የካህናት አለቆችን ለማጋለጥ ምሳሌዎችን መናገሩን ቀጠለ። በመሆኑም ሊገድሉት ፈለጉ። (ሉቃስ 20:19) ሆኖም ኢየሱስ እነሱን ማጋለጡን አላቆመም። እንዲያውም ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦

“መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ከደገሰ ንጉሥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ንጉሡም ወደ ሠርጉ የተጋበዙትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ ተጋባዦቹ ግን ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።” (ማቴዎስ 22:2, 3) ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው ስለ “መንግሥተ ሰማያት” በመናገር ነው። በመሆኑም “ንጉሡ” ይሖዋ አምላክን እንደሚያመለክት ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። የንጉሡ ልጅና ወደ ሠርጉ ድግስ የተጋበዙትስ? የንጉሡ ልጅ፣ ምሳሌውን እየተናገረ ያለው የይሖዋ ልጅ ኢየሱስ እንደሆነና ወደ ድግሱ የተጠሩት ደግሞ ከልጁ ጋር ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡትን ሰዎች እንደሚያመለክቱ መገንዘብ አይከብድም።

ወደ ሠርጉ ድግስ እንዲመጡ መጀመሪያ የተጋበዙት እነማን ናቸው? ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለ መንግሥቱ ሲሰብኩ የቆዩት ለእነማን ነው? ለአይሁዳውያን ነው። (ማቴዎስ 10:6, 7፤ 15:24) ይህ ብሔር በ1513 ዓ.ዓ. የሕጉን ቃል ኪዳን ተቀበለ፤ በመሆኑም “የካህናት መንግሥት” የመሆን አጋጣሚ መጀመሪያ የተከፈተው ለዚህ ብሔር ነው። (ዘፀአት 19:5-8) ይሁንና ብሔሩ ወደ ‘ሠርጉ ድግስ’ የተጠራው መቼ ነው? ማስረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት ይህ ግብዣ የቀረበው ኢየሱስ ስለ መንግሥተ ሰማያት መስበክ በጀመረበት ጊዜ ማለትም በ29 ዓ.ም. ነው።

ለመሆኑ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለግብዣው ምን ምላሽ ሰጡ? ኢየሱስ እንደተናገረው ወደ ሠርጉ “ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።” ከሃይማኖት መሪዎቹም ሆነ ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ፣ ኢየሱስን መሲሕና አምላክ የመረጠው ንጉሥ አድርገው አልተቀበሉትም።

ይሁንና ኢየሱስ፣ አይሁዳውያን ሌላ አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “[ንጉሡ] በድጋሚ ሌሎች ባሪያዎች ልኮ ‘ተጋባዦቹን “የምሳ ግብዣ አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። ወደ ሠርጉ ኑ” በሏቸው’ አለ። እነሱ ግን ግብዣውን ችላ በማለት አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ ሌሎቹ ደግሞ ባሪያዎቹን ይዘው ካንገላቷቸው በኋላ ገደሏቸው።” (ማቴዎስ 22:4-6) ይህ ምሳሌ  የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ የሚፈጸመውን ሁኔታ ያመለክታል። በዚያ ወቅት አይሁዳውያን ወደ መንግሥቱ የመግባት አጋጣሚ የተከፈተላቸው ቢሆንም ብዙዎቹ ግብዣውን አልተቀበሉም፤ እንዲያውም ‘የንጉሡን ባሪያዎች’ አንገላቷቸው።—የሐዋርያት ሥራ 4:13-18፤ 7:54, 58

ታዲያ ይህ በብሔሩ ላይ ምን ያስከትላል? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ንጉሡም እጅግ ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ እንዲሁም ከተማቸውን አቃጠለ።” (ማቴዎስ 22:7) አይሁዳውያን ይህ የደረሰባቸው በ70 ዓ.ም. “ከተማቸውን” ኢየሩሳሌምን ሮማውያን ባጠፏት ጊዜ ነው።

ይሁንና ይህ ብሔር የንጉሡን ጥሪ ስላልተቀበለ ሌላ ማንም አይጋበዝም ማለት ነው? ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ይህ እንዳልሆነ ያሳያል። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከዚያም [ንጉሡ] ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሠርጉ ተደግሷል፤ የተጋበዙት ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም። ስለዚህ በየአውራ ጎዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ጥሩ።’ በዚህ መሠረት ባሪያዎቹ ወደ አውራ ጎዳናዎች ሄደው ክፉውንም ጥሩውንም፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰበሰቡ፤ የሠርጉ አዳራሽም በተጋባዦች ተሞላ።”—ማቴዎስ 22:8-10

ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አሕዛብን ይኸውም በትውልድ አይሁዳዊ ያልሆኑ እንዲሁም ወደ ይሁዲነት ያልተለወጡ ሰዎችን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። የሮም ሠራዊት አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ በ36 ዓ.ም. የአምላክን መንፈስ በመቀበላቸው ኢየሱስ የጠቀሰውን መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ አጋጣሚ ተከፈተላቸው።—የሐዋርያት ሥራ 10:1, 34-48

ወደ ግብዣው ከመጡት መካከል ‘በንጉሡ’ ዘንድ ተቀባይነት የማያገኙ እንደሚኖሩ ኢየሱስ ጠቁሟል። እንዲህ አለ፦ “ንጉሡ እንግዶቹን ለማየት ሲገባ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ። በዚህ ጊዜ ‘ወዳጄ ሆይ፣ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልክ?’ አለው። ሰውየውም የሚለው ጠፋው። ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። እዚያም ሆኖ ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል’ አላቸው። የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”—ማቴዎስ 22:11-14

ኢየሱስን የሚያዳምጡት የሃይማኖት መሪዎች እሱ የተናገረውን ነገር ትርጉምም ሆነ አንድምታ ሙሉ በሙሉ ላይረዱ ይችላሉ። ያም ቢሆን በተናገረው ነገር ቅር የተሰኙ ከመሆኑም ሌላ እንዲህ እያሳፈራቸው ካለው ሰው ለመገላገል ይበልጥ ተነሳሱ።