በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

 ምዕራፍ 114

ክርስቶስ በመንግሥቱ በበጎችና በፍየሎች ላይ ይፈርዳል

ክርስቶስ በመንግሥቱ በበጎችና በፍየሎች ላይ ይፈርዳል

ማቴዎስ 25:31-46

  • ኢየሱስ የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ተናገረ

ኢየሱስ አሁንም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው፤ ስለ አሥሩ ደናግልና ስለ ታላንቱ የሚገልጹትን ምሳሌዎች ተናግሮ መጨረሱ ነው። ሐዋርያቱ ስለ መገኘቱና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት ላቀረቡለት ጥያቄ የሰጠውን መልስ እንዴት ይደመድመው ይሆን? ስለ በጎችና ፍየሎች የሚገልጽ የመጨረሻ ምሳሌ ተናገረ።

ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል” በማለት የምሳሌውን መቼት ገለጸ። (ማቴዎስ 25:31) በምሳሌው ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወተው እሱ ራሱ እንደሆነ በግልጽ ጠቁሟል። ኢየሱስ፣ ራሱን “የሰው ልጅ” በማለት በተደጋጋሚ ጠርቷል።—ማቴዎስ 8:20፤ 9:6፤ 20:18, 28

ይህ ምሳሌ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው? ኢየሱስ “ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ” እንዲሁም “በክብራማ ዙፋኑ ላይ” ሲቀመጥ ነው። የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር “በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና” እንደሚመጣ ኢየሱስ ቀደም ሲል ተናግሯል። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ‘ከመከራው በኋላ ወዲያውኑ’ ነው። (ማቴዎስ 24:29-31፤ ማርቆስ 13:26, 27፤ ሉቃስ 21:27) እንግዲያው ይህ ምሳሌ ፍጻሜውን የሚያገኘው ወደፊት ኢየሱስ በክብሩ ሲመጣ ነው። በዚያ ወቅት ምን ያደርጋል?

ኢየሱስ ‘የሰው ልጅ ሲመጣ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ’ አለ፤ ከዚያም “እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል” በማለት ተናገረ።—ማቴዎስ 25:31-33

የንጉሡን ሞገስ ያገኙትን በጎች በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከዚያም ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።’” (ማቴዎስ 25:34) በጎቹ የንጉሡን ሞገስ የሚያገኙት ለምንድን ነው?

ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ “ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል። እንግዳ ሆኜ አስተናግዳችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል። ታምሜ አስታማችሁኛል። ታስሬ ጠይቃችሁኛል።” “ጻድቃን” የተባሉት እነዚህ በጎች ከላይ የተጠቀሱትን መልካም ነገሮች ለንጉሡ ያደረጉለት በምን  መንገድ እንደሆነ ሲጠይቁ ንጉሡ “ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል” በማለት መለሰላቸው። (ማቴዎስ 25:35, 36, 40, 46) በሰማይ የታመሙ ወይም የተራቡ ስለሌሉ በጎቹ እነዚህን መልካም ነገሮች የሚያደርጉት በሰማይ አይደለም። እነዚህን ነገሮች ያደረጉት በምድር ላሉት የክርስቶስ ወንድሞች መሆን አለበት።

ንጉሡ በስተ ግራው ያደረጋቸው ፍየሎችስ ዕጣ ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከዚያም [ንጉሡ] በግራው ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ የተረገማችሁ፣ ከእኔ ራቁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው ዘላለማዊ እሳት ሂዱ። ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም። እንግዳ ሆኜ አላስተናገዳችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’” (ማቴዎስ 25:41-43) ፍየሎቹ እንዲህ ዓይነት ፍርድ የተበየነባቸው በምድር ያሉትን የክርስቶስ ወንድሞች በደግነት መያዝ ሲገባቸው እንዲህ ስላላደረጉ ነው።

ሐዋርያቱ ወደፊት የሚከናወነው ይህ ፍርድ የማይለወጥና ዘላለማዊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “[ንጉሡም] መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ይህን ሳታደርጉ መቅረታችሁ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል። እነዚህ ወደ ዘላለም ጥፋት ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”—ማቴዎስ 25:45, 46

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ተከታዮቹ ሊያስቡባቸው የሚገቡ ብዙ ነጥቦችን ይዟል፤ ይህ ትምህርት ዝንባሌያቸውንና ተግባራቸውን እንዲመረምሩ ሊያደርጋቸው ይገባል።