በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

 ምዕራፍ 78

ታማኙ መጋቢ፣ ዝግጁ ሆነህ ጠብቅ!

ታማኙ መጋቢ፣ ዝግጁ ሆነህ ጠብቅ!

ሉቃስ 12:35-59

  • ታማኙ መጋቢ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አለበት

  • ኢየሱስ የመጣው ክፍፍል ለመፍጠር ነው

ኢየሱስ፣ ሰማይ ባለው መንግሥት ውርስ የሚያገኘው “ትንሽ መንጋ” ብቻ እንደሆነ ገልጿል። (ሉቃስ 12:32) ይህ አስደናቂ ሽልማት እንደ ቀላል ነገር ሊታይ አይገባም። እንዲያውም አንድ ሰው የመንግሥቱ ወራሽ መሆን እንዲችል ትክክለኛ ዝንባሌ ማዳበሩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ኢየሱስ ጎላ አድርጎ ተናግሯል።

ኢየሱስ፣ የሚመለስበትን ጊዜ ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ ደቀ መዛሙርቱን መከራቸው። እንዲህ አለ፦ “ወገባችሁን ታጠቁ፤ መብራታችሁንም አብሩ፤ ጌታቸው ከሠርግ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁና መጥቶ በሩን ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት እንደተዘጋጁ ዓይነት ሰዎች ሁኑ። ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው ሲጠባበቁ የሚያገኛቸው ባሪያዎች ደስተኞች ናቸው!”—ሉቃስ 12:35-37

ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሳቸውን ባሪያዎች አመለካከት ደቀ መዛሙርቱ መረዳት አይከብዳቸውም። እነዚህ ባሪያዎች ጌታቸው የሚመለስበትን ጊዜ ዝግጁ ሆነው እየጠበቁ ነው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “[ጌታው] በሁለተኛው ክፍለ ሌሊትም [ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ አንስቶ እስከ እኩለ ሌሊት] ይምጣ በሦስተኛው [ከእኩለ ሌሊት እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ]፣ ዝግጁ ሆነው ሲጠብቁ ካገኛቸው ደስተኞች ናቸው!”—ሉቃስ 12:38

ይህ ምክር፣ ትጉ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ወይም አገልጋዮች መሆንን ከማበረታታት የበለጠ ትርጉም አለው። የሰው ልጅ የተባለው ኢየሱስ፣ ራሱን በምሳሌው ውስጥ ማካተቱ ይህን ያሳያል። ደቀ መዛሙርቱን “እናንተም የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 12:40) ስለዚህ ወደፊት ኢየሱስ ይመጣል። ተከታዮቹ በተለይም ደግሞ “ትንሽ መንጋ” የተባሉት ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁት ይፈልጋል።

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ ትርጉም በደንብ መረዳት ስለፈለገ “ጌታ ሆይ፣ ይህን ምሳሌ እየተናገርክ ያለኸው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም ለጴጥሮስ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ቀደም ሲል ከጠቀሰው ጋር የሚዛመድ ምሳሌ ተናገረ፦ “ጌታው ምንጊዜም የሚያስፈልጋቸውን ምግብ በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው በአገልጋዮቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ በእርግጥ ማን ነው? ጌታው ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው! እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።”—ሉቃስ 12:41-44

ቀደም ሲል በተጠቀሰው ምሳሌ ላይ “ጌታው” የሚለው አገላለጽ የሰው ልጅ የተባለውን ኢየሱስን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። ‘ታማኙ መጋቢ’ ደግሞ ‘የትንሹ መንጋ’ አባላት የሆኑትንና በሰማይ መንግሥት የሚሰጣቸውን ወንዶች ያመለክታል። (ሉቃስ 12:32) እዚህ ላይ ኢየሱስ የትንሹ መንጋ የተወሰኑ አባላት፣ ‘ለአገልጋዮቹ’ “የሚያስፈልጋቸውን ምግብ በተገቢው ጊዜ” እንደሚሰጧቸው መግለጹ ነው። ኢየሱስ እያስተማራቸውና በመንፈሳዊ እየመገባቸው ያሉት ደቀ መዛሙርትም ሆኑ ጴጥሮስ፣ የሰው ልጅ ወደፊት ተመልሶ እንደሚመጣ ከዚህ መረዳት ይችላሉ። በዚያ ጊዜም የጌታው ‘አገልጋዮች’ ይኸውም የኢየሱስ ተከታዮች በመንፈሳዊ የሚመገቡበት ዝግጅት ይኖራል።

ደቀ መዛሙርቱ ንቁ መሆንና ለዝንባሌያቸው ትኩረት መስጠት የሚያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነ ኢየሱስ በሌላ መንገድም አጉልቷል። ደቀ መዛሙርቱ ንቁ መሆን የሚያስፈልጋቸው፣ አንድ ባሪያ ቸልተኛ ሊሆን አልፎ ተርፎም የእምነት ባልንጀሮቹን እስከ መቃወም ሊደርስ ስለሚችል ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ነገር ግን ያ ባሪያ በልቡ ‘ጌታዬ የሚመጣው ዘግይቶ ነው’ ብሎ ቢያስብና ወንድና ሴት አገልጋዮችን መደብደብ እንዲሁም መብላት፣ መጠጣትና መስከር ቢጀምር የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ይመጣል፤ ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል፤ ዕጣውንም ታማኝ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ያደርገዋል።”—ሉቃስ 12:45, 46

ኢየሱስ “የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኮስ ነው” አለ። ደግሞም ይህን ፈጽሟል፤ ምክንያቱም የጋለ ውዝግብ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ጉዳዮችን ያነሳ ሲሆን ይህም የሐሰት ትምህርቶችና ወጎች ልክ በእሳት የወደሙ ያህል እንዲጠፉ አድርጓል። ይህ ደግሞ አንድነት እንዲኖራቸው በሚጠበቁ ሰዎች መካከል እንኳ መከፋፈል ይፈጥራል፤ ኢየሱስ “አባት በልጁ፣ ልጅ በአባቱ፣ እናት በልጇ፣  ልጅ በእናቷ፣ አማት በምራቷ፣ ምራት በአማቷ ላይ በመነሳት እርስ በርስ ይከፋፈላሉ” ብሏል።—ሉቃስ 12:49, 53

ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው በተለይ ለደቀ መዛሙርቱ ነው። ከዚያም እንደገና ለሕዝቡ መናገር ጀመረ። አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ፣ መሲሕ መሆኑን የሚጠቁመውን ማስረጃ ለመቀበል አሻፈረኝ በማለት ልባቸው ደንዳና መሆኑን አሳይተዋል። በመሆኑም እንዲህ አላቸው፦ “ከምዕራብ በኩል ደመና ሲመጣ ስታዩ ወዲያውኑ ‘ዶፍ ዝናብ ሊጥል ነው’ ትላላችሁ፤ እንዳላችሁትም ይሆናል። የደቡብ ነፋስ ሲነፍስ ስታዩ ደግሞ ‘ኃይለኛ ሙቀት ይሆናል’ ትላላችሁ፤ በእርግጥም ይሆናል። እናንተ ግብዞች፣ የምድሩንና የሰማዩን መልክ አይታችሁ መረዳት ትችላላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መርምራችሁ መረዳት እንዴት ተሳናችሁ?” (ሉቃስ 12:54-56) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሕዝቡ ዝግጁ አይደሉም።