በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

ምሥራች መስማት እንደሚያስደስትህ የታወቀ ነው። ደግሞም ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ የሚሆን አስደናቂ ምሥራች አለ።

ይህ ምሥራች የሚገኘው የጽንፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ከዘመናት በፊት ባስጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት የተባለው ይህ መጽሐፍ፣ ለሁላችንም የሚሆን ግሩም ምሥራች በያዙ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ ያተኩራል። እነዚህ መጻሕፍት የሚጠሩት አምላክ ዘገባዎቹን ለማስፈር በተጠቀመባቸው ሰዎች ስም ይኸውም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ተብለው ነው።

ብዙዎች እነዚህን አራት መጻሕፍት፣ አራቱ ወንጌሎች በማለት ይጠሯቸዋል። አራቱም መጻሕፍት ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ወንጌል ወይም ምሥራች ይተርካሉ፤ በሌላ አባባል አምላክ፣ መዳን እንድናገኝ ዝግጅት ያደረገው በኢየሱስ በኩል እንደሆነ እንዲሁም ኢየሱስ በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሚሆንና በእሱ በሚያምኑ ሁሉ ላይ ዘላለማዊ በረከት እንደሚያፈስ ይገልጻሉ።—ማርቆስ 10:17, 30፤ 13:13

አራት ወንጌሎች ያስፈለጉት ለምንድን ነው?

አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ትምህርቶች የሚገልጹ አራት ዘገባዎችን ያስጻፈው ለምን እንደሆነ ጥያቄ ይፈጠርብህ ይሆናል።

ኢየሱስ ስለተናገራቸውና ስላደረጋቸው ነገሮች የሚገልጹ የተለያዩ ሰዎች የጻፏቸው አራት ዘገባዎች መኖራቸው ጥቅም አለው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አራት ሰዎች አንድ ታዋቂ መምህር አጠገብ ቆመዋል እንበል። መምህሩ ፊት ለፊት የቆመው ሰው ቀረጥ ሰብሳቢ ነው። በስተ ቀኙ የቆመው ሐኪም ነው። በስተ ግራ በኩል ሆኖ የሚያዳምጠው ዓሣ አጥማጅ ሲሆን የመምህሩ የቅርብ ወዳጅ ነው። ከበስተ ኋላው ትንሽ ራቅ ብሎ ነገሮችን የሚመለከተው አራተኛው ሰው ደግሞ በዕድሜ ከሌሎቹ ያንሳል። አራቱም ሰዎች ሐቀኞች ናቸው፤ የእያንዳንዳቸውን ትኩረት የሚስበው ነገር የተለያየ ነው። አራቱም ሰዎች መምህሩ ስላስተማራቸውና ስላከናወናቸው ነገሮች ቢጽፉ በዘገባዎቻቸው ላይ የተለያዩ ክንውኖችን ወይም ዝርዝር ነጥቦችን እንደሚያሰፍሩ ግልጽ ነው። አራቱ ሰዎች ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ እንደሚመለከቱና ግባቸው አንድ እንዳልሆነ በአእምሯችን ይዘን አራቱን ዘገባዎች ስናነብ አስተማሪው ስለተናገረውና ስላደረገው ነገር የተሟላ ግንዛቤ ይኖረናል። ይህ ምሳሌ፣ ስለ ታላቁ አስተማሪ ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚገልጹ አራት ዘገባዎች መኖራቸው እንዴት እንደሚጠቅመን ያሳያል።

ምሳሌውን ስንቀጥል፣ ቀረጥ ሰብሳቢው ዘገባውን የጻፈው ለአይሁዳውያን በመሆኑ አንዳንድ ትምህርቶችን ወይም ክንውኖችን ያሰፈረው በዋነኝነት አይሁዳውያንን በሚጠቅም መንገድ  ነው። ሐኪሙ፣ ይበልጥ ትኩረት ያደረገው የታመሙ ወይም የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች በመፈወሳቸው ላይ ነው፤ በመሆኑም ቀረጥ ሰብሳቢው የጻፋቸውን አንዳንድ ክንውኖች አልዘገበም፤ አሊያም ታሪኩን ያሰፈረበት ቅደም ተከተል ይለያል። የመምህሩ የቅርብ ጓደኛ ደግሞ የመምህሩን ስሜትና ባሕርያት ጎላ አድርጎ ገልጿል። በዕድሜ ከሌሎቹ የሚያንሰው ሰው ዘገባ እጥር ምጥን ያለ ነው። ያም ሆኖ ሁሉም ትክክለኛ የሆነ መረጃ አስፍረዋል። በእርግጥም ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚያወሱ አራት ዘገባዎች መኖራቸው እሱ ስላከናወናቸው ነገሮች፣ ስለ ትምህርቶቹና ስለ ባሕርያቱ ያለንን ግንዛቤ እንደሚያሰፋልን ይህ ምሳሌ ጥሩ አድርጎ ያሳያል።

‘የማቴዎስ ወንጌል’ ወይም ‘የዮሐንስ ወንጌል’ የሚሉትን አገላለጾች መስማት የተለመደ ነው። ይህም ስህተት አይደለም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ዘገባ ‘ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጽ ምሥራች’ ይዟል። (ማርቆስ 1:1) ይሁንና ነገሩን ሰፋ አድርገን ስንመለከተው ስለ ኢየሱስ የሚገልጸው ወንጌል ወይም ምሥራች አንድ ነው፤ ይህም በአራቱ ዘገባዎች ላይ ሰፍሮልናል።

በርካታ የአምላክ ቃል ተማሪዎች በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዮሐንስ ወንጌሎች ላይ የሚገኙትን ክንውኖችና ዘገባዎች ካወዳደሩ በኋላ አንድ ላይ አጠናቅረውታል። ቴሸን የሚባለው ሶርያዊ ጸሐፊ በ170 ዓ.ም. አካባቢ እንዲህ አድርጓል። ቴሸን እነዚህ አራት መጻሕፍት ትክክለኛና በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መሆናቸውን ያምን የነበረ ሲሆን ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጸውን ዘገባ አንድ ላይ አቀናብሮ ዳያቴሳሮን የተባለ ጽሑፍ አዘጋጅቷል።

ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት የተባለው መጽሐፍ ይዘትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይሁንና የያዘው መረጃ ይበልጥ ትክክለኛና የተሟላ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ኢየሱስ ከተናገራቸው ትንቢቶች የብዙዎቹን ፍጻሜና የምሳሌዎቹን ትርጉም በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ግንዛቤ ስላለን ነው። እንዲህ ያለ ግንዛቤ ማግኘታችን እሱ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች እንዲሁም ክንውኖቹ የተፈጸሙበትን ቅደም ተከተል ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል። ከዚህም ሌላ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች፣ አንዳንድ ዝርዝር ነገሮችንና የጸሐፊዎቹን አመለካከት በተሻለ መንገድ ለመረዳት አስችለውናል። እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ ክንውን የተፈጸመበትን ቅደም ተከተል በእርግጠኝነት መናገር የሚችል የለም። ያም ቢሆን ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት በተባለው መጽሐፍ ላይ ክንውኖቹን ተፈጽመው ሊሆን በሚችልበት መንገድ ለማስፈር ጥረት ተደርጓል።

መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት

ይህን አስደሳች መጽሐፍ ስታነብ ለአንተና ለቤተሰብህ የያዘውን ዋና መልእክት ለማስተዋል ሞክር። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለሐዋርያው ቶማስ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” እንዳለው አስታውስ።—ዮሐንስ 14:6

ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት የተባለው መጽሐፍ ክርስቶስ በእርግጥም “መንገድ” የሆነው እንዴት እንደሆነ ለመገንዘብ ያስችልሃል። ወደ ይሖዋ አምላክ በጸሎት መቅረብ የሚቻለው በእሱ በኩል ብቻ ነው። በተጨማሪም ከአምላክ ጋር መታረቅ የምንችልበት መንገድ ኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 16:23፤ ሮም 5:8) በመሆኑም አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ሊቀበለን የሚችለው በኢየሱስ በኩል ወደ እሱ ከቀረብን ብቻ ነው።

ኢየሱስ “እውነት” ነው። የተናገረው ነገርም ሆነ ሕይወቱ ከእውነት ጋር የሚስማማ ነው፤ በሌላ አባባል ኢየሱስ የእውነት ተምሳሌት ነው። በርካታ ትንቢቶች “በእሱ አማካኝነት ‘አዎ’ ሆነዋል” ወይም ተፈጽመዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:20፤ ዮሐንስ 1:14) እነዚህ ትንቢቶች፣ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ኢየሱስ የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና እንድናስተውል ይረዱናል።—ራእይ 19:10

በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ “ሕይወት” ነው። ቤዛዊ መሥዋዕት በመሆን ይኸውም ፍጹም ሕይወቱን በመስጠትና ደሙን በማፍሰስ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም “የዘላለም ሕይወት” እንድናገኝ መንገድ ከፍቷል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19፤ ኤፌሶን 1:7፤ 1 ዮሐንስ 1:7) ከዚህም ሌላ በሞት ላንቀላፉ ሆኖም ትንሣኤ አግኝተው በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ሕይወት” ይሆናል።—ዮሐንስ 5:28, 29

ሁላችንም ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለውን ሚና መገንዘብና ከፍ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ይበልጥ ማወቅህን እንድትቀጥል ምኞታችን ነው።