ዮፍታሔ ለይሖዋ ምን ብሎ ቃል እየገባ ነው?

የዮፍታሔ ልጅ፣ አባቷ የገባውን ቃል መፈጸም ቀላል ባይሆንላትም ይህን አድርጋለች

በሥዕሉ ላይ ያለችውን ልጅ አየሃት?— ይህች ልጅ ዮፍታሔ የተባለ ሰው ልጅ ናት። መጽሐፍ ቅዱስ ስሟን ባይናገርም ይህች ልጅ አባቷንና ይሖዋን ደስ እንዳሰኘች ይገልጻል። እስቲ ስለዚህች ልጅና ስለ አባቷ ስለ ዮፍታሔ የሚገልጸውን ታሪክ እንመልከት።

ዮፍታሔ ጥሩ ሰው ሲሆን ልጁን ሁልጊዜ ስለ ይሖዋ ያስተምራት ነበር። በተጨማሪም ዮፍታሔ ጠንካራ ሰው እንዲሁም ጎበዝ መሪ ነበር። በመሆኑም እስራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ጋር ጦርነት ሲያደርጉ መሪያቸው እንዲሆን ዮፍታሔን ጠየቁት።

ዮፍታሔም በጦርነቱ ለማሸነፍ እንዲረዳው ወደ አምላክ ጸለየ። ይሖዋ በጦርነቱ እንዲያሸንፍ ከረዳው ወደ ቤቱ ሲመለስ እሱን ለመቀበል ከቤት አስቀድሞ የሚወጣውን ሰው ለይሖዋ ለመስጠት ቃል ገባ። መጀመሪያ የወጣው ሰው ቀሪ የሕይወት  ዘመኑን በሙሉ በአምላክ ማደሪያ ድንኳን ውስጥ እየኖረ አምላክን ያገለግላል። የማደሪያው ድንኳን የሚባለው በዚያ ዘመን ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩበት ቦታ ነው። ዮፍታሔ በጦርነቱ አሸነፈ! ወደ ቤት ሲመለስ አስቀድሞ ከቤት የወጣው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?—

አዎ፣ በመጀመሪያ የወጣችው የዮፍታሔ ሴት ልጅ ነበረች! ያለችው ልጅ ደግሞ እሷ ብቻ ናት፤ በተሳለው መሠረት እሷን ወደ ማደሪያው ድንኳን መላክ ነበረበት። በዚህ ጊዜ ዮፍታሔ በጣም አዘነ። ይሁንና ለይሖዋ ቃል እንደገባ አስታውስ። ልጁም ወዲያውኑ እንዲህ አለችው፦ ‘አባቴ ሆይ፣ ለይሖዋ ቃል ገብተሃል፤ ስለዚህ ቃልህን መጠበቅ አለብህ።’

የዮፍታሔን ልጅ ጓደኞቿ በየዓመቱ እየሄዱ ይጠይቋት ነበር

የዮፍታሔ ልጅም ልትሄድ መሆኑ አሳዝኗታል። በማደሪያው ድንኳን፣ ባል ማግባት ወይም ልጆች መውለድ አትችልም። ይሁን እንጂ አባቷ የገባውን ቃል ለመፈጸምና ይሖዋን ለማስደሰት ትፈልግ ነበር። ባል ከማግባት ወይም ልጅ ከመውለድ አስበልጣ የምትመለከተው ይህንን ነበር። በመሆኑም ቤቷን ትታ ወደ ማደሪያው ድንኳን በመሄድ ቀሪ ሕይወቷን በዚያ አሳለፈች።

ይህች ልጅ ያደረገችው ነገር ይሖዋንና አባቷን እንዳስደሰታቸው ይሰማሃል?— ምንም ጥያቄ የለውም! አንተም ታዛዥ ከሆንክና ይሖዋን የምትወድ ከሆነ እንደ ዮፍታሔ ሴት ልጅ መሆን ትችላለህ። እንዲህ ካደረግክ ወላጆችህንም ሆነ ይሖዋን በጣም ታስደስታለህ።

የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ