በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ትምህርት 5

ሳሙኤል ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ያደርግ ነበር

ሳሙኤል ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ያደርግ ነበር

ሳሙኤል ከትንሽነቱ ጀምሮ የሚኖረውና የሚያገለግለው በማደሪያው ድንኳን ነበር፤ የማደሪያው ድንኳን ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩበት ቦታ ነው። ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን ማገልገል የጀመረው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? እስቲ በመጀመሪያ የሳሙኤል እናት ስለሆነችው ስለ ሐና እንመልከት።

ሐና ልጅ እንዲኖራት ብትፈልግም ለረጅም ጊዜ ልጅ መውለድ አልቻለችም። በመሆኑም ወደ ይሖዋ በመጸለይ ልጅ እንዲሰጣት ለመነችው። ሐና ልጅ ከወለደች፣ ልጁን በማደሪያው ድንኳን እንዲኖርና እንዲያገለግል ለመስጠት ቃል ገባች። ይሖዋም ጸሎቷን ስለሰማ ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙንም ሳሙኤል አለችው። ሐና ቃል በገባችው መሠረት ሳሙኤል ሦስት ወይም አራት ዓመት ሲሆነው በማደሪያው ድንኳን አምላክን እንዲያገለግል ወደዚያ ወሰደችው።

በማደሪያው ድንኳን የሚያገለግለው ሊቀ ካህን ዔሊ ነበረ። ሁለቱ ወንዶች ልጆቹም ካህናት ሆነው በዚያ ያገለግሉ ነበር። የማደሪያው ድንኳን አምላክ የሚመለክበት ቦታ በመሆኑ በዚያ ያሉ ሰዎች ጥሩ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የዔሊ ልጆች መጥፎ ነገር ይፈጽሙ ነበር። ሳሙኤል የሚያደርጉትን ይመለከት ነበር። ታዲያ ሳሙኤል የዔሊን ልጆች መጥፎ ምሳሌ ተከትሎ ይሆን?— በፍጹም፣ ከዚህ ይልቅ ልክ ወላጆቹ እንዳስተማሩት ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጉን ቀጠለ።

ዔሊ ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ የነበረበት ይመስልሃል?— ተግሣጽ ሊሰጣቸው እንዲሁም በአምላክ ቤት እንዳያገለግሉ ሊከለክላቸው ይገባ ነበር። ዔሊ ግን ይህን አላደረገም፤ በመሆኑም ይሖዋ በእሱና በሁለቱ ልጆቹ ላይ ተቆጣ። ይሖዋ ሁሉንም ለመቅጣት ወሰነ።

ሳሙኤል የይሖዋን መልእክት ለዔሊ ነገረው

ከዕለታት አንድ ቀን ሳሙኤል ተኝቶ ሳለ ስሙ ሲጠራ ሰማ። ሳሙኤልም ወደ ዔሊ ሮጦ ሄደ፤ ዔሊ ግን ‘እኔ አልጠራሁህም’ አለው። ይህ ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ ተደገመ። ሁኔታው ለሦስተኛ ጊዜ ሲከሰት፣ ዔሊ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘ስምህ ሲጠራ ከሰማህ “ይሖዋ ሆይ፣ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” ብለህ መልስ።’ ሳሙኤልም እንደተባለው አደረገ። ከዚያም ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘ቤተሰቡ በፈጸመው መጥፎ ድርጊት የተነሳ  እንደምቀጣቸው ለዔሊ ንገረው።’ ሳሙኤል ይህን መልእክት ለዔሊ መናገር ቀላል የሚሆንለት ይመስልሃል?— በፍጹም! ይሁን እንጂ ሳሙኤል ፍርሃት ቢያድርበትም ይሖዋ የነገረውን አድርጓል። በኋላም ይሖዋ የተናገረው ነገር ተፈጸመ። የዔሊ ልጆች የተገደሉ ሲሆን ዔሊም ሞተ።

ሳሙኤል ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ሌሎች ሰዎች መጥፎ ነገር በሚያደርጉበት ጊዜም እንኳ ሳሙኤል ትክክለኛውን ነገር ማድረጉን ቀጥሏል። አንተስ? ልክ እንደ ሳሙኤል ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ትጥራለህ? እንደዚህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋንም ሆነ ወላጆችህን ታስደስታለህ።

የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ