በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

 ትምህርት 2

ርብቃ ይሖዋን ማስደሰት ትፈልግ ነበር

ርብቃ ይሖዋን ማስደሰት ትፈልግ ነበር

ርብቃ ይሖዋን የምትወድ ሴት ነበረች። ባሏ፣ ይስሐቅ ይባላል። እሱም ይሖዋን ይወዳል። ርብቃና ይስሐቅ የተገናኙት እንዴት ነው? ርብቃ፣ ይሖዋን ለማስደሰት እንደምትፈልግ ያሳየችውስ እንዴት ነው? እስቲ መጀመሪያ ስለ ርብቃ ባል ስለ ይስሐቅ እንመልከት።

ይስሐቅ የአብርሃምና የሣራ ልጅ ነው። የሚኖሩት በከነዓን ምድር ሲሆን የዚያ አገር ሰዎች ይሖዋን አያመልኩም ነበር። ይሁን እንጂ አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ይሖዋን የምታመልክ ሴት እንዲያገባ ይፈልግ ነበር። ስለዚህ አብርሃም፣ አገልጋዩን (ኤሊዔዘርን ሳይሆን አይቀርም) ለይስሐቅ ሚስት እንዲፈልግለት ወደ ካራን ላከው፤ ከአብርሃም ዘመዶች አንዳንዶቹ በካራን ይኖሩ ነበር።

ርብቃ ግመሎቹን ውኃ ለማጠጣት ስትል ብዙ ደክማለች

ኤሊዔዘር ከሌሎች የአብርሃም አገልጋዮች ጋር ጉዞ ጀመረ። ካራን ለመድረስ ረጅም ርቀት መጓዝ ነበረባቸው። ምግብና ስጦታዎችን በአሥር ግመሎች ላይ ጭነው ነበር። ኤሊዔዘር ለይስሐቅ ሚስት የምትሆነውን ሴት የሚመርጠው እንዴት ነው? ኤሊዔዘርና ሌሎቹ የአብርሃም አገልጋዮች ካራን ሲደርሱ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ አሉ፤ ኤሊዔዘር፣ ሰዎች ውኃ ለመቅዳት ወደዚያ እንደሚመጡ ያውቅ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ሲል ወደ ይሖዋ ጸለየ፦ ‘ውኃ አጠጪኝ የምላት ወጣት ለእኔም ሆነ ለግመሎቼ ውኃ ከሰጠችኝ ይህች ሴት አንተ የመረጥሃት እንደሆነች አውቃለሁ።’

በዚህ ጊዜ ወጣቷ ርብቃ ወደ ውኃ ጉድጓዱ መጣች። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ርብቃ እጅግ ውብ እንደሆነች ይናገራል። ኤሊዔዘር ውኃ እንድትሰጠው  ሲጠይቃት ‘እሺ፣ ለአንተ ውኃ እሰጥሃለሁ፤ ለግመሎችህም እቀዳላችኋለሁ’ አለችው። እስቲ አስበው! የተጠሙ ግመሎች በጣም ብዙ ውኃ ይጠጣሉ፤ በመሆኑም ርብቃ ግመሎቹን ለማጠጣት ወደ ጉድጓዱ ብዙ ጊዜ መመላለስ ነበረባት። ርብቃ፣ ምን ያህል ተግታ እየሠራች እንደሆነ በሥዕሉ ላይ ይታይሃል?— ኤሊዔዘር፣ ይሖዋ ጸሎቱን እንደመለሰለት ሲመለከት በጣም ተገረመ።

ኤሊዔዘር፣ ለርብቃ በርካታ የሚያማምሩ ስጦታዎችን ሰጣት። እሷም ኤሊዔዘርንና ሌሎቹን አገልጋዮች ቤተሰቦቿ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ከዚያም ኤሊዔዘር፣ አብርሃም ወደዚያ የላከው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ ጸሎቱን እንዴት እንደመለሰለት ተናገረ። የርብቃ ቤተሰቦችም ልጃቸው ይስሐቅን ብታገባ ደስ እንደሚላቸው ገለጹ።

ርብቃ ከኤሊዔዘር ጋር ወደ ከነዓን በመሄድ ይስሐቅን አገባች

ይሁን እንጂ ርብቃ ይስሐቅን ማግባት የምትፈልግ ይመስልሃል?— ርብቃ፣ ኤሊዔዘርን ወደዚያ የላከው ይሖዋ እንደሆነ አውቃለች። በመሆኑም ቤተሰቦቿ ወደ ከነዓን ሄዳ ይስሐቅን ማግባት ትፈልግ እንደሆነ ሲጠይቋት ‘አዎን፤ እሄዳለሁ’ ብላ መለሰች። ከዚያም የዚያኑ ዕለት ከኤሊዔዘር ጋር ሄደች። ከነዓን ሲደርሱም ርብቃ ይስሐቅ አገባች።

ርብቃ ይሖዋን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆኗ ተባርካለች። ከበርካታ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ የተወለደው በእሷ ዘር በኩል ነው። አንተም እንደ ርብቃ ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆንክ ይሖዋ ይባርክሃል።

የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ