በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ የትርጉም ቡድን ውስጥ የሚያገለግል ወንድም አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ሲቀረጽ። በስተ ቀኝ፦ አንድ ባልና ሚስት በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀ ቪዲዮ ሲመለከቱ

ጥር 25, 2022
ደቡብ አፍሪካ

የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቀረቡ

ሁለት ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ ወጡ

የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቀረቡ

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች መብት የሚሟገቱ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ ደረጃቸውን የጠበቁ ቪዲዮዎችን በማውጣት መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ይህ የሆነው ኅዳር 15, 2021 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ የሚገኙት የገላትያ እና የኤፌሶን መጻሕፍት በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ ከወጡ በኋላ ነው። እስካሁን ድረስ አሥር የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ ወጥተዋል። አራት ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ደግሞ እስከ ሚያዝያ 2022 ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሁሉም በ​jw.org እና በ​JW Library Sign Language አፕሊኬሽን ላይ ይገኛሉ።

የትምህርት አሰጣጥ ባለሙያ እና የምዕራባዊ ኬፕ መንግሥት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሚና ስቴይን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “በምልክት ቋንቋ ቪዲዮውን የተቀረጹትን ሰዎች ማየት በጣም ያስደስተኛል፤ የተዘጋጀበት መንገድ ደረጃውን የጠበቀ እና ጥራት ያለው በመሆኑ እነሱንም ሆነ ድርጅቱን ማመስገን እፈልጋለሁ።”

የኤስዋቲኒ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቦንጋኒ ማካማ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውና የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች መረጃ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ስላመቻቹ እናመሰግናቸዋለን።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “[መስማት የተሳናቸው ሰዎች] በራሳቸው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት መስማት የተሳናቸው ሰዎች በሚገባቸው ቋንቋ በማዘጋጀታቸው እናመሰግናቸዋለን። በምልክት ቋንቋ 66ቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሚወጡበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።”

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ 450,000 ገደማ ሰዎች አሉ። በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መስማት የተሳናቸው ወይም የመስማት ችግር ያለባቸው 283 አስፋፊዎች አሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉት ጥረት ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን ጨምሮ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እያገኙ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:4