በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ማርክ ሳንደርሰን በክዋንጋሊ፣ በሴፑላና እና በሴጽዋና የወጡትን መጽሐፍ ቅዱሶች ሲያሳይ

መጋቢት 10, 2021
ደቡብ አፍሪካ

በደቡብ አፍሪካ ሦስት መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

በደቡብ አፍሪካ ሦስት መጽሐፍ ቅዱሶች ወጡ

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ክዋንጋሊ፣ ሴፑላና እና ሴጽዋና ተናጋሪ የሆኑ አስፋፊዎች መጋቢት 7, 2021 ልዩ ስጦታ አግኝተዋል። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን አስቀድሞ በተቀረጸ ንግግር አማካኝነት፣ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በክዋንጋሊ እና ሴፑላና እንዲሁም የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሴጽዋና ቋንቋዎች መውጣቱን አብስሯል። አስፋፊዎቹ ይህን ልዩ ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የተከታተሉ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱሶቹን የኤሌክትሮኒክ ቅጂ ማግኘት ችለዋል።

ክዋንጋሊ

ሦስት ተርጓሚዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን የትርጉም ሥራውን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ወስዶበታል። የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ከ240 የሚበልጡ አስፋፊዎች በግል ጥናታቸውና በአገልግሎታቸው የሚጠቀሙበት ለማንበብ ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አግኝተዋል።

ሴፑላና

አንድ ዓመት ተኩል በፈጀው በዚህ የትርጉም ሥራ ላይ ስድስት ተርጓሚዎች ተካፍለዋል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ 374 ሴፑላና ተናጋሪ አስፋፊዎች አሉ።

አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “አገልግሎት ስንወጣ ብዙ ጊዜ የምንጠቀመው በሴፔዲ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች አንድን ጥቅስ ከማብራራታችን በፊት የአንድ ወይም የሁለት ቃላትን ትርጉም ማብራራት ነበረብን። አሁን ግን በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ልክ ጥቅሱን ስናነብላቸው ትርጉሙን ወዲያውኑ ይረዱታል።”

ሴጽዋና

የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ለማውጣት አራት ዓመት ገደማ ወስዷል። ስድስት ተርጓሚዎች በሥራው ተካፍለዋል። ሴጽዋና ተናጋሪ የሆኑ ከ5,600 በላይ አስፋፊዎች አሉ።

አንድ ተርጓሚ በሴጽዋና ስለተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አስፋፊዎች በአገልግሎት ላይ አስቸጋሪ ቃላትን ከማብራራት ይልቅ ክህሎታቸውን በማሻሻል ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል። በተጨማሪ ለጥናት የሚረዳ ግሩም መሣሪያ ነው። ሰንጠረዦቹ፣ ካርታዎቹ፣ ሥዕሎቹ እንዲሁም የቃላት መፍቻው አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በዓይነ ሕሊናቸው መሣል እንዲችሉ ይረዷቸዋል።”

እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም ሆኑ ምሥራቹን የሚሰብኩላቸው ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዲችሉ ይረዷቸዋል። በዛሬው ጊዜ ለምናገኘው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በእጅጉ አመስጋኞች ነን!—ኢሳይያስ 65:13