በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሚኮላ ቦዤዶሞቭ በዩክሬን ባለው በዶኔስክ ግዛት፣ ክራማቶርስክ ውስጥ የሚገኘው ባቡር ጣቢያ በቦምብ በወደመበት ወቅት ሕይወቱ አልፏል

ግንቦት 4, 2022
ዩክሬን

ፍቅር የተንጸባረቀበት ተግባር

“ይሄ የመጨረሻ ጉዞው ነበር”

ፍቅር የተንጸባረቀበት ተግባር

ዩክሬን ውስጥ በምትገኘው በዶኔስክ ግዛት የሚደረገው ጦርነት እየተፋፋመ ሲሄድ ወንድም ሚኮላ ቦዤዶሞቭ ወደ ክራማቶርስክ ተመላልሶ በመሄድ ብዙ ሰዎች ከጦርነቱ አካባቢ እንዲወጡ ረድቷል።

ሚኮላ እና ኒና ቦዤዶሞቭ

የሚያሳዝነው ወንድም ሚኮላ ሚያዝያ 8, 2022 በክራማቶርስክ፣ ዶኔስክ ግዛት የሚገኘው ባቡር ጣቢያ በቦምብ በተደበደበበት ወቅት ሕይወቱ አለፈ።

በወቅቱ ከሞቱት ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መካከል የ58 ዓመቱ ወንድም ሚኮላ እና ሌላ አንዲት እህት ይገኙበታል። በተጨማሪም ጉዳት ከደረሰባቸው ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መካከል አንድ ወንድም ነበር። ከጥቃቱ የተረፉ ወንድሞች እንዳሉት ሁለት ከባድ ፍንዳታዎች የተከሰቱ ሲሆን የብረት ፍንጥርጣሪዎችም ነበሩ።

ለ32 ዓመታት በትዳር አብራው የኖረችው ኒና እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ምንጊዜም የሌሎችን ጥቅም የሚያስቀድም ሰው ነበር። በዕድሜ የገፉና ታማሚ የሆኑ ወንድሞችን መርዳት በጣም ያስደስተው ነበር። ወደ ክራማቶርስክ የሚያደርገው ጉዞ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ አስጊ እየሆነ መጣ። ይሄ የመጨረሻ ጉዞው ነበር።”

ሁለቱም የተጠመቁት በ1997 ነው። ሚኮላ ለበርካታ ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ በታማኝነት አገልግሏል። ኒና የወንድሞችና የእህቶች ፍቅርና ድጋፍ አልተለያትም። “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚያጽናኑ ቃላትን በመናገር አበረታተውኛል” ብላለች።

ኒና እንደ ኢሳይያስ 40:28-31 ያሉት ጥቅሶችም እንዳጽናኗት ተናግራለች። “ይሖዋ ኃይሌ እንዲታደስ አድርጓል። የይሖዋን ፍቅር በላቀ ሁኔታ ማጣጣም ችያለሁ። ከዚህ በፊት እንዲህ ስላለው ፍቅር በጽሑፎቻችን ላይ ነበር የማነበው። አሁን ግን ራሴ ቀምሼዋለሁ” ብላለች።

ኒናንም ሆነ በጦርነቱ ምክንያት የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡትን ሁሉ በጸሎታችን እናስባቸዋለን። ይሖዋ ደግፎ እንደሚይዛቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 20:2