በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የራማፖ ሕንፃዎች ሲጠናቀቁ ምን እንደሚመስሉ የሚያሳይ ንድፍ

ሚያዝያ 27, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የዋናው መሥሪያ ቤት የራማፖ ፕሮጀክት

የመግቢያው መንገድ እንዲሠራ ፈቃድ ተገኘ፤ የመጨረሻውን ፕላን ለማጸደቅ እየተሠራ ነው

የመግቢያው መንገድ እንዲሠራ ፈቃድ ተገኘ፤ የመጨረሻውን ፕላን ለማጸደቅ እየተሠራ ነው

መጋቢት 8, 2022 በራማፖ የሚካሄደው የግንባታ ሥራ የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴ ከተክሲዶ ከተማ የፕላን ቦርድ ወሳኝ ፈቃድ አገኘ። ፈቃዱ ወደ ራማፖ ፕሮጀክት የሚወስደውን መግቢያ ለመሥራትና ለማስፋፋት የሚያስችል ነው። በተጨማሪም ወንድሞቻችን ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሚያስችለውን የመጨረሻውን ፈቃድ ከራማፖ ከተማ የፕላን ቦርድ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው። *

የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው አስተባባሪ የሆነው ወንድም ሮበርት ማክሬድሞንድ እንዲህ ብሏል፦ “የፕሮጀክቱ ዕቅድ እንደተጀመረ ወደ ራማፖ የሚወስደው የመኪና መንገድ መሠራት እንዳለበት ተገንዝበን ነበር። በቅርቡ ያገኘነው ይህ ፈቃድ መንገዱን ለማስፋት የመንገድ ተቋራጮችን ለመቅጠር ያስችለናል፤ ይህ ደግሞ በመንገዱ ላይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል። የመንገድ ተቋራጮቹ ይህን ሥራ እስከ ፊታችን መስከረም መጨረሻ ድረስ እንደሚያጠናቅቁ ይጠበቃል። በሌላ በኩል ደግሞ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በዚህ ጎዳና ላይ ያለውን ታሪካዊ የድንጋይ ድልድይ እያደሱ ነው።”

በከፊል የታደሰው የድንጋይ ድልድይ፤ ድልድዩ የሚገኘው ከግንባታ ስፍራው መግቢያ አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ነው

በግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው ውስጥ የሚያገለግለው ወንድም ጌሪ ስትራዶስኪ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ፈቃድ በማግኘታችን በጣም ተደስተናል። ለቀሪው ፕሮጀክት የፕላን ፈቃድ በቅርቡ እንደምናገኝ እንጠብቃለን። ፈቃዱን እንዳገኘን የሕንፃ ተቋራጮቹ አካባቢውን የማጽዳትና የማስተካከል ሥራ ይጀምራሉ፤ ይህ ሥራ እስከ 2022 መጨረሻ ድረስ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲህ ማድረግ ከቻልን ደግሞ እስከ 2023 አጋማሽ ድረስ ፈቃደኛ ሠራተኞች መጥተው በፕሮጀክቱ ላይ መሳተፍ ይችላሉ።”

ፕሮጀክቱ ስላለበት ሁኔታ በመስማታችን ደስ ብሎናል፤ ለሥራው የይሖዋ መንፈስ አመራር እንዳይለየንም እንጸልያለን።—ዘካርያስ 4:6

^ በራማፖ ያለን መሬት ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሉት ኦሬንጅ እና ሮክላንድ አውራጃዎች ውስጥ የሚገኝ ነው። በመሆኑም የግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው ከተክሲዶ ከተማ ፕላን ቦርድ እና ከራማፖ ከተማ ፕላን ቦርድ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበታል