በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ፉሚኮ ታኬሃራ እና ልጇ ናኦኪ በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ JW ዜና ላይ የወጡትን ዜናዎች እያነበቡ ሲወያዩ

መጋቢት 8, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ወላጆች ልጆቻቸው ፈተናን በድፍረት እንዲጋፈጡ ለመርዳት JW ዜና ላይ የሚወጡትን ዜናዎች እየተጠቀሙ ነው

ወላጆች ልጆቻቸው ፈተናን በድፍረት እንዲጋፈጡ ለመርዳት JW ዜና ላይ የሚወጡትን ዜናዎች እየተጠቀሙ ነው

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ብዙ ወላጆች የልጆቻቸውን እምነት ለማጠናከር JW ዜና ላይ የሚወጡትን ዜናዎች እየተጠቀሙ ነው።

በጃፓን የምትኖረው እህት ፉሚኮ ታኬሃራ እና የ12 ዓመቱ ልጇ ናኦኪ JW ዜና ላይ የሚወጡትን ዘገባዎች እያነበቡ ይወያያሉ። ፉሚኮ እና ናኦኪ በእነዚህ ርዕሶች ላይ የወጡትን የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ፎቶግራፎች አትመው ግድግዳ ላይ ይለጥፏቸዋል። ፉሚኮ እንዲህ ብላለች፦ “እያንዳንዳቸውን በስም ጠቅሰን እንጸልይላቸዋለን። ይሖዋ አገልጋዮቹ እስር ቤት ቢሆኑም እንኳ ደስተኛ እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው ማወቃችን ያጽናናናል። በወንድሞቻችን ፊት ላይ ደስታ ይነበባል። የእነሱ ጥሩ ምሳሌነት ልጄ በትምህርት ቤት ለይሖዋ ታማኝ እንዲሆን ረድቶታል።”

የወንድም ኪላንኮ ዛኑ ቤተሰብ ለመስበክ የሚያስችል ድፍረት ለማዳበር JW ዜና ላይ በሚወጡት ዜናዎች ላይ ሲወያዩ

በኮት ዲቩዋር የሚኖረው ወንድም ኪላንኮ ዛኑ ሁለት ልጆች አሉት፤ ኪላንኮ “በየቀኑ jw.org​ን ከፍቼ JW ዜና ላይ አዲስ ዜና ወጥቶ እንደሆነ አጣራለሁ” ብሏል። ኪላንኮ ብዙ ጊዜ በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ ዜናዎቹን ያካትታቸዋል። ኪላንኮ፣ ሰባት ዓመት የሆነውን ልጁን ማትያስን ጨምሮ ቤተሰቡ በሙሉ ስደትን በድፍረት ከተቋቋሙ ወንድሞቻችን ብዙ ትምህርት እንዳገኙ አስተውሏል።

ማትያስ አብረውት ለሚማሩ ልጆች መመሥከር ያስፈራው ነበር። ኪላንኮ እንዲህ ብሏል፦ “የቤተሰብ አምልኮ ስንጨርስ ማትያስ ‘ከዚህ በኋላ መስበክ አልፈራም!’ ብሎ በደስታ ተናገረ።”

በኢንዶኔዥያ የሚኖረው ሆምስ ሲማቱፓንግ የተባለ አባት፣ ለሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ ባለመስጠታቸው ምክንያት ከትምህርት ቤት ስለተባረሩ በኢንዶኔዥያ የሚኖሩ ልጆች የወጡትን ሁለት ዜናዎች ከልጆቹ ጋር አነበበ።

የወንድም ሆምስ ሲማቱፓንግ ቤተሰብ በትምህርት ቤት የገለልተኝነት አቋማቸውን ስለጠበቁ ልጆች በሚገልጽ ዜና ላይ ሲወያዩ

ወንድም ሲማቱፓንግ እንዲህ ብሏል፦ “ሁለቱ ልጆቻችንም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ፈተና በትምህርት ቤት ያጋጥማቸዋል። ለሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ እንዲሰጡ፣ ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘምሩ እንዲሁም በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ አስተማሪዎቻቸውና አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች ሁልጊዜ ጫና ያሳድሩባቸዋል። በዚህም የተነሳ ልጆቻችን ትምህርት ቤት መሄድ የሚፈሩበት ጊዜ ነበር።”

ወንድም ሲማቱፓንግ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “በቤተሰብ አምልኳችን ላይ በሁለቱ ዜናዎች ላይ ከተወያየን በኋላ ልጆቻችን ሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ ያለንን አቋም በድፍረት ማስረዳት ችለዋል። አሁን ከትምህርት ቤት የመባረር ጉዳይ ከልክ በላይ አያስጨንቃቸውም።”

በብራዚል የምትኖረው እህት ሌዲ ኔሪ ፓሶስ እንዲህ ብላለች፦ “ልጃችን ፔድሮ የአምስት ወይም የስድስት ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት በትምህርት ቤት ልደት ከማክበር ጋር የተያያዘ ፈተና አጋጥሞት ነበር።” እህት ፓሶስ ልጇን እንዴት መርዳት እንደምትችል ስታስብ፣ JW ዜና ላይ የወጡትን ፈተናን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ስላደረጉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች የሚገልጹ ተሞክሮዎች አስታወሰች። እንዲህ ብላለች፦ “ልጃችን ሊያጋጥሙት የሚችሉ ሁኔታዎችን በቤተሰብ አምልኳችን ላይ እንለማመድ ነበር፤ ይህም ልጃችን ትምህርት ቤት ውስጥ ልደት ሲከበር ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲያውቅ ረድቶታል።” በዚህ መልኩ ልምምድ ማድረጋቸው ፔድሮ ለእምነቱ ጥብቅና እንዲቆም አዘጋጅቶታል።

ወንድም ፓሶስ እና ባለቤቱ ልጃቸው ለእምነቱ ጥብቅና እንዲቆም ለማሠልጠን በ​JW ዜና ሲጠቀሙ

JW ዜና ላይ የሚወጡት ዘገባዎች ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን በእጅጉ እንደሚያጠናክርና እንደሚንከባከብ ያረጋግጡልናል። ፈተናዎች ሲደርሱብን መጽናት እንድንችል ‘በደስታና በመንፈስ ቅዱስ እንደምንሞላ’ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለን።—የሐዋርያት ሥራ 13:50-52